በሱማሌ የጸጥታ አካሉ መግባት መረጋጋትን እየፈጠረ ነው---የጎሳ መሪዎች ሰብሳቢ

68
አዲስ አበባ ሐምሌ 30/2010 የፀጥታ አካሉ ሱማሌ ክልል መግባት በመጀመሩ  መረጋጋት እየፈጠረ መሆኑን የክልሉ የጎሳዎች ሰብሳቢ ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሐመድ ዶል አስታወቁ። የጎሳ ሰብሳቢው እንዳሉት የመከላከያ አካሉ ወደ ክልሉ እንዲገባ ቀደም ብለው ጥሪ በማቅረብ ላይ እንደነበሩም ገልፀዋል። ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሐመድ ዶል ከኢዜአ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት አሁን የመከላከያ አካላት ወደ ክልሉ መግባት የጀመረ ሲሆን ይህን ተከትሎም መረጋጋት መታየት መጀመሩን ገልፀዋል። በክልሉ ካለፈው ቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ ከየት መጣ በማይባል የጥቃት ኃይል ሳቢያ በተፈጠረው እንቅስቃሴ ሶማሊኛ ቋንቋ የማይናገሩ ነዋሪዎች ላይ ግድያ የመፈፀም፣ የቤት ማቃጠልና ንብረት መዝረፍ ተግባር ተፈፅሟል ብለዋል። የሁከቱ መነሻ ፓርላማው ከአገሪቱ ሊገነጠል ነው በሚል ወሬ መነሻ ያልታወቁ የተደራጁ ኃይሎች መከላከያ ሰራዊት ላይ ድንጋይ በመወርወር የተጀመረ ግርግር እንደነበርም ገልፀዋል። በወቅቱም መከላከያ ምንም ተኩስ ሳያሰማ ወደ ካምፕ መግባቱንም ጠቁመዋል። ይህ የሁከት ኃይል ቀድሞ የተደራጀ ኃይል በመሆኑ ቶሎ መፍትሄ መስጠት አልተቻለም ብለዋል። ከአቅም በላይ በመሆኑም ጉዳዩን የመከላከያ ሰራዊት እንዲቆጣጠረው ለመንግስት አካላት ጥሪ አቅርበናል ብለዋል። ከሁከቱ በኋላ የአገር ሽማግሌዎችና ኢማሞችን በመሰብሰብ በቤተክርስቲያን ተሰብስቦ ያለውን ህዝብ የማረጋጋትና ያልተዘረፉ ቀሪ ተቋማትንም የመጠበቅ ስራ መስራታቸውንም ገልፀዋል። በተጨማሪም ዛሬ ጠዋት ከከተማው ነዋሪ በማሰባሰብ ከቤቱ ወጥቶ በቤተክርስቲያን ተጠልሎ ላለው ህብረተሰብ የምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል። በሁከቱ የተጎዱ አካላትን የማረጋጋትና ወደ ወደቤታቸው የመመለስ ስራ ላይም ከሽማግሌዎችና ከአካባቢው ሰዎች ጋር መምከራቸውን ጠቁመዋል። የተዘረፈው ሃብትም በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ሃብቱ እንዲመለስ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል። በቀጣይም የሁከቱ መሪዎችና ተሳታፊዎችን በማጣራትና ለሚመለከተው አካል አሳልፎ በመስጠት በጋራ እንደሚሰሩም ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም