ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው... አንቶንዮ ጉተሬዝ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው... አንቶንዮ ጉተሬዝ
ሐምሌ 3 ቀን 2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ባሳዩት ቁርጠኝነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ አደነቁ፡፡
ጉቴሬዝ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በስልክ ከጠቅላይ ሚንስትር አቢይ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይታቸውም በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ እንደነበር ነው የዋና ጸኃፊው ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ሀይል ትላንት በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት፡፡
በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የረድኤት ድርጀቶች በትግራይ ክልል ለሚያደርጉት የሰብዓዊ እርዳታ አስፈለጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል የመገናኛ እና የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን በአፋጣኝ ለማስጀመርም ቃል የገቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ቃል መግባታቸው አድንቀዋል፡፡
መንግስት በክልሉ ለሚካሄደው የእርሻ ስራ አርሶ አደሮች በነጻነት እንዲያከናዉኑ የተናጠል የተኩስ አቁም መደረጉ እና የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የበረራ አገልግሎት መፈቀዱ የሚበረታታ መሆኑን ጉቴሬዝ ተናግረዋል፡፡