ቀጥታ፡

ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጠላትነት የሚተያዩበት ወቅት አልፏል--አቶ መለሰ አለሙ

ሐምሌ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጠላትነት የሚተያዩበት ወቅት አልፎ በሀሳብ የሚፎካከሩበትና በሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ የሚሰሩበት አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ ተከፍቷል ሲሉ የአዲስ አበባ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በጋራ በመሆን በየካ ክፍለ ከተማ ሚሊኒዬም ፓርክ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተክለዋል።

በመርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ተቋማት ዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ እና የተፎካካሪ ፓርቲ አባላቶች ተሳትፈዋል።

የአዲስ አበባ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ እንደገለጹት፤ ገዥው ፓርቲና የተፎካካሪ ፓርቲዎች በጠላትነት የሚተያዩበት ወቅት አልፎ በሀሳብ የሚፎካከሩበትና በሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ የሚሰሩበት አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ ተከፍቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ምእራፍ በማጠናከር የጋራ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች በትብበር በመስራት፤በሀሳብ ደግሞ በመፎካከር ኢትዮጵያን የመገንባት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካሄዱት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ "ኑ ኢትዮጵያን እናልብስ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄን የበለጠ እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ዕድገት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

በዴሞክራሲያዊ ፉክክር መንግስት ለመሆን የሚያሸንፈውም ሆነ በውድድሩ የተፎካከሩ ፓርቲዎች ለአገር ልማት የበኩላቸውን ሚና የመወጣት ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አባላቶች በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአንድ አካል የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገራዊ የልማት መርሃ ግብሮች ላይ በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያውያን ”ኑ ኢትዮጵያን እናልብስ” በሚል ሃሳብ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በመርሃ ግብሩም ስድስት ቢሊዮን ችግኞች በሀገር ውስጥ ለመትከል እንዲሁም አንድ ቢሊዮን ችግኞችን ደግሞ ለጎረቤት ሀገራት ለመላክ እቅድ መያዙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም