ለሀገር እና ህዝብ …

71

በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

የሁሉም እምነት ተቋማት የአስተምህሮ መነሻ እና መድረሻ ሰላም እና አብሮነት እንደሆነ የየእምነቱ መሪዎች እና መምህራን የሚገልጹ ሲሆን ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት እንደሆነም ይናገራሉ። ሰላም ከእያንዳንዱ ግለሰብ የሚመነጭና እሴቱም ለሀገር የሚተርፍ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ። የሀገር ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለውም እያንዳንዱ ዜጋ ለሰላም ትርጉም ሲሰጥና ሲተገብረው ብቻ ነው።  

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካተኮሩባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መንግስት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማወጁን የተመለከተ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ የሕወሐት ቡድን ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ መንግስትን ጨምሮ በተለያዩ አካላት የተደረጉ ጥረቶችን መለስ ብለው አስታውሰዋል፡፡ ከሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ያፈነገጠው የህወሃት ቡደን ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በመሰባሰብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶችና መፈናቀሎች እንዲከሰቱ ተዋናይ በመሆን መስራቱን አንስተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ሀገራዊ ለውጡን ባለመቀበል መቀሌ መሽጎ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ ተግባራት ወደ መፈጸም መሸጋገሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች ናቸው። በዚህም በመላ ሀገሪቱ ዜጎች ተረጋግተው የእለት ተእለት ኑሮአቸውን እንዳይመሩ ከማድረጉም ባሻገር በክልሉ ህገ-ወጥ ምርጫ በማካሄድ አፈንጋጭነቱን በይፋ አሳይቷል። በመጨረሻም  በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጦር በመክፈት ክህደትን ፈጽሟል። 

የሽብር ቡድኑ ከጥፋት ተግባሩ እንዲቆጠብ ለማድረግ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባለሀብቶች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም የወዳጅ ሀገራት መሪዎች እና ዲፕሎማቶች ጭምር ችግሮችን በውይይትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም እምቢተኛ ሆኗል። የሰላም ጥሪ ያነገቡ እናቶች ጭምር በክልሉ በመገኘት ላቀረቡት ጥሪ ስላቅ የተሞላበት ምላሽ ነበር የሰጣቸው፡፡  

ቡድኑ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ይለኩሳቸው የነበሩ የጥፋት እንቅስቃሴዎች ሳይበቃው ከሀያ ዓመታት በላይ የሰሜኑን ህዝብ እና ድንበር ሲጠብቅ፣ የትግራይን ህዝብ ችግሮች ለመቅረፍ ሌት ተቀን ሲለፋ የነበረውን መከላከያ ሰራዊት ክብሩንና ዝናውን በማይመጥን መልኩ ጥቃት በመሰንዘር ለሰላም ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለው አሳይቷል።

የህወሃት ቡድን ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ትልቅ ድፍረት እና ንቀት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን የተናገረው በራሱ አንደበት ነበር። በዚህ ወቅት ነበር መንግስት የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሲባል በቡድኑ ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ እዲወሰድ ውሳኔ ያሳለፈው፡፡ መንግስት ባስቀመጠው ግልጽ ግብ መሰረት በሶስት ሳምንት ውስጥ ቡድኑን በመበተን፣ ከፍተኛ መሳሪያዎችን በማምከንና በመቆጣጠር እንዲሁም የቡድኑን ከፍተኛ አመራሮች በመደምሰስ እና በቁጥጥር ስር በማዋል ተልዕኮውን ስለመፈጸሙ ጉዳዩን ሲመሩ የነበሩ አካላት በተለያዩ ጊዜያት መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

መንግስት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻውን እንዳጠናቀቀ ወዲያው ክልሉን ወደ መልሶ ማልማት እና ግንባታ ምዕራፍ በመግባት በቡድኑ የወደሙ የመሰረተ-ልማት አውታሮችን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡና ለችግር ለተዳረጉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን በማቅረብ ችግሮች እንዳይባባሱ ለማድረግ ጥረት አድርጓል። ለዚህም ባለፉት ወራት ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ለእርዳታ፣ ለመንግስት አገልግሎት ማስቀጠልና ለመሰረተ ልማት ግንባታ እንዳዋለ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ይሁንና የሽብር ቡድኑ ወደ ኢ-መደበኛ የውጊያ ስልት በመግባት በከተሞች ውስጥ ራሱን ከነዋሪዎች ጋር በማመሳሰል ጥቃት መፈጸሙን አላቋረጠም። የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ኢ-መደበኛ ውጊያ ተቋማዊ በሆነ መልኩ የማይመራ፣ የሚለይበት የደንብ ልብስ የሌለው እንዲሁም ከጦር አውድ ውጪ ህዝብን እንደምሽግ በመጠቀም አሳቻ ሁኔታና ጊዜ እየጠበቀ በተለያዩ አካላት ላይ ጥቃት ፈጽሞ የሚሰወር፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ በጉልበት የሚገታ ቡድን ነው። የሕወሓት የሽብር  ቡድንም ሲፈጽም የሰነበተው ይኸው ድርጊት ነው። 

መንግስት በትግራይ ክልል በሕወሓት ቡድን እየተፈጸመ ያለው ተግባር ከገመገመ በኋላ የተናጠል የተኩስ ማቆም ፖለቲካዊ ውሳኔ ላይ ደርሷል። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት በሀገሪቱ ሰላምን ማስቀደም ዓላማ ያደረገ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው “የሽብር ቡድኑ በህዝብ ውስጥ በመሆን ቀን ቀን ሰላማዊ ማታ ማታ ታጣቂና ተዋጊ እንዲሁም ቡድኑ ያስታጠቃቸው ሰዎች ሲገድሉ ድል፣ እነርሱ ሲገደሉ ደግሞ ንጹሃን ተገደሉ በሚል ለራሱ የፕሮፓጋንዳ ግብዓትነት እየተጠቀመበት መሆኑን፤ በሂደት ይህ ቡድን በህዝቡ ውስጥ በመደበቅ አመቺ ጊዜ ሲያገኝ ሰራዊቱን የሚያጠቁ ታጣቂዎች እየበዙ በመምጣቱ ምክንያት በመከላከያ ሰራዊት አይን ሁሉንም ህዝብ በተለይ ወጣቶችን በሙሉ ጥቃት ይፈጽሙብኛል በሚል ስጋት በሚያያቸው ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ከመጀመሩ በፊት የተወሰነ ውሳኔ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ከቡድኑ እኩይ ተግባር አኳያ ክልሉን ማብቂያ ወደ ሌለው ግጭት እንዲያመራ ከማድረግ እና ጥቁር ታሪክ ጽፎ ከማለፍ ይልቅ ለክልሉ ህዝብ የጥሞና ጊዜ በመስጠት የፌዴራል መንግስት ሀላፊነት የተሞላበት ውሳኔ ወስኗል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት የተኩስ አቁም ውሳኔው ያስፈለገበት ምክንያት ክረምት እየገባ በመሆኑ የትግራይ አርሶ አደር ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ለተረጂዎች ያለምንም ችግር እንዲደርስ ወቅቱን የሚመጥን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ነው።  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ባልደረባ የሆኑት አቶ ዳንኤል ማሞ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ የትግራይ ህዝብ በክልሉ የነበረውን ሁኔታ  መከላከያ ሰራዊት ከክልሉ ከወጣ በኋላ ከሚኖረው ሁኔታ ጋር በማነጻጸር እንዲያስተውል ዕድል ይሰጣል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፍልስፍና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰሜ የትግራይ ህዝብ በአንድ የተሳሳተ የፖለቲካ ቡድን መታለል እንደሌለበት ገልጸው ከተሳሳተ ትርክት እንዲወጣም አሳስበዋል።

መንግስት ለሰላም ሲል የወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን እንደሽንፈት የቆጠረው የህወሓት ቡድን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላም ንፁሐንን መግደል ተያይዞታል። ሰራዊቱ ከወጣ ሁለት ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ላይ ሲያገለግሉ የነበሩትን፣ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን፣ በራያ አዘቦ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ንጹሃንን እንዲሁም የኤርትራ ስደተኞችን መግደሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከጦርነት አትራፊ የሚሆን ህዝብም ይሁን ሀገር የለም። የትግራይ ህዝብ ለሀገርና ለህዝብ ሰላም ሲባል የተወሰደው የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ በጥሞና ጊዜው በጸጥታ ችግር ወቅት  የተዳከመውን ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያገግም የሚያስችል ውሳኔ መወሰን ይኖርበታል መልእክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም