የፀጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ድል ከፍ ያደረገ መሆኑን ምሁራን አስታወቁ

ጎንደር፤ ሐምሌ 2/2013(ኢዜአ) በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ድል ከፍ ያደረገና የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን መፍትሄ እንዲያገኝ አጽንኦት የሰጠ መሆኑን በጎንደርና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን አስታወቁ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፍልስፍና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰሜ እንዳሉት፤ የፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴው ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ መወሰኑ ለአፍሪካ ህብረት የሰጠውን ትልቅ ግምት ያሳያል፡፡  

ኢትዮጵያን የወከሉት በፀጥታው ምክር ቤት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ከፍ ባለ ደረጃ ከማስጠበቃቸው በላይ በዓለም መድረክ የላቀ ዲፕሎማሲያዊ ድል የተቀዳጁበት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረት በኩል በቀጣይ የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር ውጤታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ የተፋሰሱን ሃገራት በማስተባበር ለጋራ ተጠቃሚነት የጀመረችውን ጥረት እንድታጠናክርም ጠቁመዋል፡፡

"የግብጽ እና ሱዳን ጥያቄ አብሮ የመልማትና የማደግ መርህን የሚቃረን ሆኖ በመገኘቱ የፀጥታው ምክር ቤት ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲከናወን ውሳኔ ማሳለፉ ተገቢነት አለው'' ያሉት ደግሞ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ መኳንንት ዱቤ ናቸው፡፡

ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈግ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት በኩል ለሚካሄደው ቀጣይ ድርድር ራሷን ልታዘጋጅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ዲፕሎማቶችን በበቂ ሁኔታ በማዘጋጀት ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከወዲሁ መስራት አለባት" ሲሉም አክለዋል።

አቶ መኳንንት እንዳመለከቱት፤ በሀብትም ሆነ በፖለቲካው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ መንግስት በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ  የጀመረውን የዲፕሎማሲ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

ሌላው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ስለሺ ዋለልኝ በበኩላቸው፤ "የሦስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲካሄድ መወሰኑ ኢትዮጵያ ላቀረበችው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የሰጠ ታሪካዊ ውሳኔ ነው'' ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽንና የአፍሪካ አንድነት መስራቾች ከሆኑ ጥቂት ሀገራት ግንባር ቀደም መሆኗን አስታውሰው፣ "የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ የታሰበልንን ማዕቀብ የቀለበሰ ነው" ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

የምክር ቤቱ ውሳኔ የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካዊያን ለመፍታት እንደሚቻል ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያም ይህን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም አፍሪካዊያን ወዳጆቹዋን ከጎኗ ማሰለፍ እንደሚጠበቅባት ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ምሁሩ ገለጻ፤ የግብጽና አጋሮቿ ወቅታዊ ጫናዎች ኢትዮጵያ በጂኦ ፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዳትሆን የሚደረግ ጥረት ነው።

ኢትዮጵያዊያን የወቅቱ ፈተና ለመሻገር አንድነትና ህብረታቸውን ማጠናከር  በጋራ መረባረብ እንዳለባቸው  አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም