የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ በሱማሌ ክልል የተፈጠረውን ሁከት ለማረጋጋት ወደ ክልሉ አንዲገቡ መንግስት ትዕዛዝ ሰጠ

126
አዲስ አበባ ሐምሌ 30/2010 የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ከዛሬ ጀምሮ በሱማሌ ክልል የተፈጠረውን ሁከት የማረጋጋት ኃላፊነት እንዲወጣ መንግስት ትዕዛዝ ሰጠ። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ማምሻውን እንዳስታወቀው በሱማሌ ክልል የተፈጠረው ችግር ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን በማስታወቁ ነው የፀጥታ ኃይሉ እንዲገባ የተወሰነው። የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የተጀመሩ አገራዊ የለውጥ ተግባራት በተሳካ ሁኔታ እየሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት በሱማሌ ክልል ሁከት ተከስቶ መጠነ ሰፊ ጉዳት ደርሷል። የክልሉ ህዝቦች ለተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተጋለጡ ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር የተናገሩት ኃላፊ ሚንስትሩ፤ የፌዴራል መንግስት ችግሩን በሚፈታበት ሁኔታ ላይ ከክልሉ አመራሮች ጋር ሲመክር መቆየቱንም ገልፀዋል። አሁን በክልሉ የተፈጠረው ችግር በጥቂት አመራሮች አማካኝነት መሆኑንም አክለዋል። የተወሰኑ የክልሉ ልዩ ፖሊስ አባላት  ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ መንገድ መዝጋትን በመሳሰሉ ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ እንደነበሩም አቶ አህመድ ገልፀዋል። በክልሉ በተፈጠረው ሁከት የሰው ህይወትን ጨምሮ የፋይናንስና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል። የክልሉ መንግስት የተከሰተውን ሁከት ለማረጋጋት ከአቅሙ በላይ በመሆኑ የፌደራል የጸጥታ መዋቅር ወደ አካባቢው እንዲገባ መጠየቁን ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ የአገር መከላከያ ሰራዊት ክልሉን የማረጋጋቱን ተግባር እንዲያከናውን  ትዕዛዝ ተሰጥቶታል ብለዋል። የክልሉ ፖሊስም ለአገር መከላከያ ሰራዊትና ለፌደራል ፖሊስ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ለህብረተሰብ ሰላም ዘብ መሆኑን እንዲያስመሰክርም ጥሪ አቅርበዋል። በክልሉ የደረሰውን ዝርዝር ጉዳት የሚያጣራና የሚመረምር የፌደራል ጸጥታና የፍትህ አካላት ያሉበት ኮሚቴ መዋቀሩንም ሚንስትሩ ገልፀዋል። ከሁከቱ ጋር በተያያዘ የደረሰውን ጉዳት መጠን በተመለከተ በቀጣይ ዝርዝር መረጃ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል። ኮሚቴው በሁከቱ የተሳተፉ አካላት ላይ  አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ ለህግ እንደሚያቀርባቸውም ጨምረው ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም