የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደ ለማጠናቀቅ ይሰራል- የኤርፖርቶች ድርጅት

ሚዛን ሐምሌ 1/2013 (ኢዜአ ) በቤንች ሸኮ ዞን 926 ሚሊዮን ብር ወጪ ለመገንባት የተጀመረውን የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ገለጸ።

ድርጅቱ የአውሮፕላን ማረፊያውን  ግንባታ በተያዘው ሳምንት አስጀምሯል።

የድርጅቱ ተወካይ አቶ ሙላቱ ይርዳው  እንደተናገሩት ፤ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የአካባቢውን ህብረተሰብ የአውሮፕላን ማረፊያ እንዲሰራለት ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የነበረውን  ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ያደርጋል።

አራት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ በሁለት  ዓመት  ተኩል ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ግንባታው የሚካሄድበትን ሥፍራ ከአራት ዓመታት በፊት ነጻ በማድረግ ፈቃደኝነታቸውን  ቢያሳዩም፤ ግንባታው ባለመጀመሩ ቅሬታ አሳድሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም መንግሥት ግንባታው እንዲጀመር ያስተላለፈውን ውሳኔ  ተከትሎ አርሶ  አደሮች  በይዞታው ላይ የሚገኘውን  ሰብል ፈጥነው በመሰብሰብ ያሳዩት ትብብር  ለሌሎች አካባቢዎች ተምሳሌት ያደርጋቸዋል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን  በበኩላቸው፤ የዞኑ አስተዳደር ለግንባታው ስኬታማነት ከሥራ ተቋራጩ  ድርጅቱ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ መጀመር የህዝቡ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን  አረጋግጠዋል።

ይህም ለአካባቢው ምጣኔ ሀብታዊ እድገትና  የቱሪዝም ልማትን ያነቃቃል  ተብሎ  እንደሚጠበቅም ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ ተቋራጭ   ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን ቸርነት፤ የአካባቢው ማህበረሰብ  ለአውሮፕላን ማረፊያው  ግንባታ ያለውን ፍላጎትና ተነሳሽነት አድንቀዋል።

ለግንባታ ሥራው የሚያስፈልጉ መሳሪዎች  ወደ አካባቢው እየተጓጓዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ግንባታውን በጥራትና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉንም  አቶ  ሳምሶን ተናግረዋል።

የሚዛን አማን ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ሻንቆ ጋኪናንስ  ለኢዜአ በሰጡት  አስተያየት  አውሮፕላን ማረፊያው ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ በመሆኑ  ግንባታው  ለፍጻሜ  እንዲደርስ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ  ሰኔ 10/ 2013 የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም