የመብሰያን ጊዜን ከ6 ወደ 1 ሰዓት የሚያወርድ ማብሰያ (ስቶቭ) እየተመረተ ነው... የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

97

ሐምሌ 1/2013(ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የደገፈው ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅት የመብሰያን ጊዜን ከ6 ሰዓት ወደ አንድ ሰዓት የሚያወርድ ማብሰያ (ስቶቭ) እያመረተ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አህመዲን መሃመድ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ እና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍሬህወይት ወልደሃና የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

ድርጅቱ ከቡና አተላና ገለባ፣ ከጫት ገረባ፣ ሳጋቱራና ከመሳሰሉት የቆሻሻ ውጋጆች ሃይል መስራት የሚያስችል እና ይህንን የሚጠቀም ስቶቭ እያመረተ ይገኛል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ማብሰያዎች ከአካባቢ ጋር የሚስማሙና ፍጆታን የሚቀንሱ ናቸው ተብሏል።

ከቆሻሻ ውጋጅ የሚገኘውን ሃይል እና ማብሰያውን የሚያመርተው ድርጅቱ በቀን እስከ 200 የሚደርስ "ቋያቶን" የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ስቶቭ እያመረተ መሆኑም ተገልጿል።

የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ፀጋየ ነጋ "የቋያቶንን ንድፍ እቃውን መፈብረክና ለቋያቶን የሚሆን ተቀጣጣይ በአንድ ላይ በማምረት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ውስጥ ብቸኛ ነን" ብለዋል።

ተቀጣጣዩ ለማብሰያነት ካገለገለ በኋላ ወደ ከሰልነት የሚቀየር ሲሆን ድርጅቱ ከሰሉን ከደንበኛው ድጋሚ በመግዛት ስራ ላይ ያውለዋል ነው የተባለው።

በብዛት ለምግብነት የሚሰራን ወጥ ምሳሌ ያደረጉት ፕሮፌሰሩ፤ 100ሊትር ወጥን ለማብሰል 6 ሰዓት ይፈጅ የነበረውን የማብሰያ ጊዜ ወደ 1 ሰዓት የሚያወርድ ማብሰያም መስራታቸውን ጠቁመዋል።

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ እየሰራ የሚገኘው ድርጅቱ፤ በፓርኩ ውስጥ የተሰጠውን የመስሪያ ቦታ ልቀቅ በመባሉ ምክንያት ስጋት እንዳደረበት ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ ተቋማቸው ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን የሚደግፍበት "የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች አዋጅ" (startup proclamation) አዘጋጅቶ መጽደቁን እየተጠባበቀ መሆኑንና ይህ አዋጅ እንዲህ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታም ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ድርጅቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የመስሪያ ሼድ ኪራይን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግለት እንደቆየም ተገልጿል።

ከሰሃራ በታች 600ሚሊየን አካባቢ የስቶቭ ፍላጎት ያለ ሲሆን በዘርፉ የተሰማሩ ጥቂት ተቋማት ብቻ መሆናቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም