ዜጎች ማህበራዊ የትስስር ገፆችን በመጠቀም ሀገርን ለማሻገር ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

85

ድሬዳዋ፤ ሰኔ 29/2013(ኢዘአ) ዜጎች ማህበራዊ የትስስር ገፆችን ተጠቅመው ሀገር ለማሻገር ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

በድሬዳዋ ለፖለቲካ ድርጅቶችና ለሲቪክ ማህበራት በማህበራዊ ትስስር ገፆች ዕውቀትን እንዲያጎለብቱ ለማገዝ ካርድ የተባለ ሀገር በቀል የሲቪክ ማዕከል ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ዶክተር ዮናስ አሸኔ በመድረኩ ባደረጉት ገለጻ ፤ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ሀገርን ለማሻገርና የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዋጿቸው የጎላ ነው፡፡

በዲጂታል ዓለም ውስጥ የማህበራዊ ትስስር ገፆች የፖለቲካ መድረክ በመሆን እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፍተኛ የሃሳብ ማንሸራሸሪያ የሆነውን ይህን ዘርፍ ዜጎች ዛሬ ሀገርን ለማሻገርና ነገን የተሻለች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የነገሰባት ሀገር ለትውልድ ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ሀገር በቀል የዕርቅ፣የሰላም፣ የአንድነትና የውይይት ትውፊቶችን ወደዚህ መድረክ በማምጣት ሰላምና አንድነትን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባም ምሁሩ አመልክተዋል፡፡

" ዘርፉ ስለ ነገ አዲስ ነገር ለማሰብ ፣ ለሰላም፣ ለአዲስ የፖለቲካ አውድ መፈጠር ፣ችግሮች በውይይት ለመፍታት፣ ሁከትን ለማስቀረት ያግዛል" ብለዋል፡፡

የማህበራዊ ትስስር ገፆች ምንነትና አጠቃቀም ግንዛቤ በየደረጃው ለሚገኙ ዜጎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ አክቲቪስቶችና ወጣቶች መስጠት እንደሚገባ ዶክተር ዮናስ አስገንዝበዋል፡፡

የማህበራዊ ትስስር ገፆች አጠቃቀምን ለማጎልበት የሚሰራው ካርድ የተባለው ሀገር በቀል ድርጅት የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አጥናፉ ብርሃኔ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚቀርቡ የሃሰት መረጃዎችና የውሸት ዜናዎች ለመቆጣጠር ከፌስ ቡክና ሌሎች ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚካሄድ ሁከትና ግጭትን ለማስቀረት ጥረት እያደረገ ነው ያሉት አቶ አጥናፉ መድረኩ በዘርፉ ኃላፊነት ለመወጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ ለማገዝ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮች የማህበራዊ ትስስር ገፆች ዕውቀት ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለው ሥርዓተ ትምህርት እንዲካተት ማገዝ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የተሻለ ትውልድና ሀገር ለመገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ማህበራዊ ትስስር ገፆችን በጥንቃቄና በአግባቡ መጠቀም የሀገር ከፍታንና ዴሞክራሲን ለማሳደግ እንደሚበጅ ገልጸዋል፡፡

ምሁራንና ሌሎችም ዜጎች ሀገርን ለማሻገር ሚና መጫወትና ሁከት ፈጣሪዎችን በማጋለጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም