በአማራ ክልል በክረምቱ የተያዘውን የሰብል ልማት ግብ ለማሳካት ህዝቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደረግ ጥሪ ቀረበ

1059

ባህርዳር፤ ሰኔ 29/2013 በአማራ ክልል በክረምቱ ወቅት ከአራት ሚሊዮን 500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በሰብል ለማልማት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ህዝቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በግብርና፣ አረንጓዴ አሻራና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤  በዘንድሮው ክረምት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ጦም የሚያድር መሬት እንዳይኖር ከወዲሁ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።

በማንኛውም አስቸጋሪ ወቅት ሆነን ለግብርና ልማቱ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ከመስራት ወደ ኋላ አንልም ብለዋል።

በመኸር ልማቱ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ  በግብአትነት የሚያገለግል 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር  ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩና በዘርፉ  ለተሰማሩ ባለሃብቶች መሰራጨቱን አስታውቀዋል።

በዘንድሮው የእርሻ ስራ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን በማዳበር አረምን በጋራ ለማስወገድና ተባይን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በምርት ዘመኑ  4 ሚሊዮን 500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በሰብል ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ግብ መሳካት መላ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ  ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ በተጓዳኝም  በደብረ ማርቆስ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ2 ቢሊየን በላይ ችግኝ በመትከል ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ህዝቡ አውቆ የድርሻውን እንዲወጣም አመልክተዋል።

የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ በመትከል ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እንዲውል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

እንዲሁም ተፈናቃዮች  ቀድሞ ወደ ነበሩበት ቦታ በመመለስ  የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረት  ውጤታማ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም በቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉትን መመለስ ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉተን ለመመለስም በምክትል ርዕሰ መስተዳደሮች የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም ለማጠናቀቅ በተደረገው እንቅስቀሴ የሀገራችን ህዝብ ያኮራ ድል ተመዝግቧል ብለዋል።