የኢትዮ-ኤርትራ የወዳጅነት ዝግጅት በሪያድ ተከበረ

1621

ሪያድ ሃምሌ 30/2010 የኢትዮ-ኤርትራ የወዳጅነትና የሰላም ማብሰሪያ መርኃ ግብር በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተካሄደ።

ዝግጅቱ በሪያድ የኢትዮጵያና የኤርትራ ማኅበረሰብ ማኅበራት በጋራ ነው የተዘጋጀው ተብሏል።

በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠባባቂ ጉዳይ ፈጻሚ አቶ አብዱረሂም መሃመድ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አገራቱ የተፈራረሙት የሠላምና ሥምምነት የመሪዎቹን ብስለት የሚያሳይ ነው።

ስምምነቱ ካለምንም ሦስተኛ ወገን ግፊትና ጣልቃ ገብነት መፈረሙ እንዲሁም በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ከፍተኛ ድጋፍ የተቸረው መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ሥምምነቱ የቂም በቀልን ግንብ አፍርሶ የፍቅር ድልድይ በመገንባት ለአገራቱ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ ቀንድና ለዓለም አገራት ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀና በአርያነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።

ይህም “የቀድሞ ወዳጅነታችንን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ በመሆኑ ሁላችንም በአዲስ መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ ለመሥራት  የምናበስርበት ቀን ነው” ብለዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የኤርትራ አምባሳደር መሃመድ ዑመር መሃመድ በበኩላቸው አገራቱ የደረሱበት የሠላም ሥምምነት የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ጥቅም የሚያስከብር ነው።

ሌሎች አገራት ይህንን የሠላምና የወዳጅነት እርምጃ እንደ ምሳሌ ሊወስዱት እንደሚገባና አገራቱ ለቀጣይ አጋርነታቸው ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በበዓሉ ተሳታፊ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያንም በአገራት የተፈረመው ስምምነት የአገራቱን ሕዝቦች በማቀረራብ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም የሰላም ጅማሮ በፍቅርና በአንድነት መንፈስ ዳር እንዲደርስ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተቀማጭነታቸውን በሪያድ ያደረጉ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች፣ የሁለቱ አገራት ዲፕሎማቶችና የማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።