ባላድና ወተት እና የወተት ውጤቶች ማምረቻ ኩባንያ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት እንደሚፈልግ ገለጸ

134

ሰኔ 28/2013(ኢዜአ) የኳታሩ ባላድና ወተት እና የወተት ውጤቶች ማምረቻ ኩባንያ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት እንደሚፈልግ ገልጿል።

ኩባንያው በእንስሳት እርባታ፣ በወተት እና የወተት ውጤቶች አመራረት፣ እንዲሁም የምርት አስተሻሸግ ሂደት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች በኳታር የሚገኙት የኢትዮጵያ ኤምባሲው ዲፕሎማቶች ጎብኝተዋል፡፡

ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በዚሁ ዘርፍ በኢንቨስትመንት ለመሠማራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

በጉብኝቱ ወቅትም በኢትዮጵያ ወተት እና የወተት ውጤቶችን ለማምረት አመቺ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዳለ በዲፕሎማቶቹ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በኳታር እ.ኤ.አ በ 2017 በገልፍ አገሮች የተጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ የአገሪቱን የምግብ ፍጆታ በአገር ውስጥ ለማምረት ወደ ስራ የገባው ኩባኒያው፣ በአሁኑ ወቅት ኳታር በወተት እና የወተት ውጤቶች ሙሉ በሙሉ ራሷን እንድትችል ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።

ባላድና በ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ካ.ሜ መሬት ላይ በእንስሳት እርባታ እና በወተት ውጤቶች ማምረት በመሰማራት በዘርፉ ከፍተኛ እውቀት እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች እየተመራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ያስመዘገበ በቀጠርና በቀጠናው ቀዳሚ ድርጅት መሆኑም ተገልጿል።

ኩባኒያው ወደ ምርት ከተሸጋገረ በጥቂት ዓመታት ውጤት ያስቆጠረ መሆኑም ተጠቅሷል።በአሁኑ ወቅት ከውጭ አገራት አስገብቶ በሚያረባቸው ላሞች በቀጠር ያለውን 90 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የወተት ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ምርቱን ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ ላይ እንደሚገኝ መረጃው ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም