ብሔራዊ ሎተሪ በአዲስ አበባ በ29 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ሕንጻ አስመረቀ

100
አዲስ አበባ ሐምሌ 30/2010 ብሔራዊ ሎተሪ በአዲስ አበባ በ29 ሚሊዮን ብር ለሎተሪ ትኬት ማከማቻና ለቢሮ አገልግሎት ያስገነባውን ሕንጻ አስመረቀ። አስተዳደሩ በዋናው መስሪያ ቤት የቢሮና ትኬቶች ማከማቻ ቦታዎች ችግርን ለማቃለል በየወሩ ከ150 ሺህ ብር በላይ ያወጣ ነበር። 29 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን ህንፃ ግንባታ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም በስራ ተቋራጮች ችግር ምክንያት በስድስተኛ ዓመቱ ተጠናቋል። የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገረመው ጋርጄ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በአስተዳደሩ የእድገት ፍጥነት ልክ የቢሮና የትኬቶች ማከማቻ ቦታዎች አለመዘጋጀታቸው አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ፈተና ሆነው ነበር። በዋናው መስሪያ ቤት ችግሩን ለማቃለል ሁለት የስራ ሂደት ቢሮዎችና ሁለት መጋዘኖች በመከራየት ሲሰራ እንደነበርም ተናግረዋል። በአዳማ፣ በዲላና በባሌ የክልል ቅርንጫፎችም ቢሮዎች መገንባታቸውን ገልፀው በሃዋሳ፣ በመቀሌ፣ በድሬዳዋና በሻሸመኔ ከተሞች ህንፃ ለመገንባት የዲዛይን ስራዎች እየተጠናቀቀ መሆኑንም ገልጸዋል። የህንፃው ግንባታ የአስተዳደሩን የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም ማህበራዊና ልማታዊ ተሳትፎ የሚያጠናክር መሆኑንም አብራርተዋል። በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ገብረእግዚአብሄርና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎችና ጉምሩክ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ወንድወሰን ወጋየሁ ተገኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም