በጉጂ ዞን ከ52 ሚሊዮን በላይ ምርጥ የቡና ችግኝ ተተከለ

77
ነገሌ ሀምሌ 30/2010 በጉጂ ዞን በተያዘው የክረምት ወቅት ከ52 ሚሊዮን በላይ ምርጥ የቡና ችግኝ ተተክሎ እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን የዞኑ ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም ልማት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ገለጸ። በጽህፈት ቤቱ የዘርፉ ባለሙያ አቶ አብዲሳ ለማ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዞኑ በሚገኙ ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ከተዘጋጀው 57 ሺህ 521 የቡና ችግኝ ውስጥ እስካሁን  52 ሚሊዮን 283 ሺህ የሚሆነው ተተክሏል። ችግኙ የተተከለው በዞኑ 10 ወረዳዎች ለቡና ልማት ተስማሚ በሆነ 16 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ ነው። የቡና ችግኝ ተከላው አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ባለሙያው እንዳሉት ዘንድሮ የተዘጋጀው የቡና ችግኝ ካለፈው ዓመት በ9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብልጫ አለው። በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋት በየዓመቱ ከ48 እስከ 55 ሚሊዮን የቡና ችግኝ በ157 የገጠር ቀበሌዎች እንደሚተከል ነው የተናገሩት። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በዞኑ ከተተከለው 105 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ውስጥ 89 ሚሊዮን የሚሆነው  ጸድቋል። በልማቱም ከ19 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል። ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል የሻኪሶ ወረዳ ነዋሪ አቶ አየለ ኤዴማ በሰጡት አስተያየት ዓምና ለተከሉት 500 የቡና ችግኝ ተገቢ እንክብካቤ በማድረጋቸው በመልካም ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ከሁለት ሄክታር መሬት ላይ በየዓመቱ 22 ኩንታል እሸት ቡና በመልቀም ለገበያ እንደሚያቀርቡ የገለፁት አቶ አየለ ዘንድሮም ልማቱን ለማስፋፋት በግማሽ ሄክታር ይዞታቸው ላይ 630 የቡና ችግኝ መትከላቸውን ገልዋል፡፡ አቶ በቀለ ሮቤ በበኩላቸው እስካሁን በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ቡና እንደሚያለሙ ገልጸው ልማቱ አዋጪ በመሆኑ ዘንድሮ ልማቱን በሁለት እጥፍ ለማሳደግ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም