በሰሜን ወሎ 324 ሺህ ወጣቶችን ያሳተፈ የክረምት በጎ የፈቃድ አገልግሎት ለማካሄድ እየተሰራ ነው

60

ወልድያ 28/10/2013 በሰሜን ወሎ ዞን 324 ሺህ ወጣቶችን ያሳተፈ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የወጣቶች ጉዳይ ድጋፍና ክትትል ባለሙያ አቶ ዮርዳኖስ ደምሌ ለኢዜአ እንደገለጹት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመሰማራት ፍላጎቱ እያደገ መጥቷል።

በዘንድሮ ክረምት 324ሺህ ወጣቶችን ያሳተፈ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱን ለማስጀመር በየወረዳው  ተሳታፊ ወጣቶችን የመመዝገብ ስራ በመገባደድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሀምሌ 1 እስከ ነሀሴ 30 ቀን 2013 ዓም  በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የጤና ግንዛቤ ፈጠራ፣ የከተማ ጽዳትና ውበት እንዲሁም የችግኝ ተከላ ተግባራት እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።

የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ የስራ አጥ መረጃ ማሰባሰብና ሌሎች ተግባራት እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።

በዞኑ ለሚገኙ 64 ሺህ ተፈናቃዮች የሚውል የምግብ እህል፣ አልባሳትና የትምህርት ቁሳቁስ የማሰባሰብ ስራም የአገልግሎቱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚከናወኑ ተግባራት 28 ሚሊዮን ብር  የመንግስት ወጪን ለማዳን ታሳቢ መደረጉን ባለሙያው አስታውቀዋል።

በዞኑ ባለፈው  ክረምት 206 ሺህ ወጣቶችን በማሳተፍ በተካሄደ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ስራዎች መከናወናቸውን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም