ዓለም አቀፉ የቼዝ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ የቼዝ ፌዴሬሽን ቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርግ ነው

977

አዲስ አበባ ሃምሌ 30/2010 ዓለም አቀፉ የቼዝ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ የቼዝ ፌዴሬሽን የመጫወቻ ዕቃዎች ድጋፍ ሊያደርግ ነው።

ፌዴሬሽኑ አራት መቶ የቼዝ ቦርድ ከነ ጠጠሩና አንድ መቶ የቼዝ ሰዓቶችን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የቼዝ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የሚደረገው ድጋፍ በመጠን ከዚህ በፊት ከተደረገው ይበልጣል።

ዓለም አቀፍ የቼዝ አሰልጣኝ በሆኑት ግራንድ ማስተር ኢፍስትራቲዮስ ግሪቫስ በኩል የመጫወቻ ዕቃዎቹ እንደተገኙም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የቼዝ ስፖርትን ለማሳደግ ተመሳሳይ ድጋፎችን በማድረግ ከአገሪቱ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

መስከረም 2011 ዓ.ም በጆርጂያ ባቱሚ ከተማ በሚካሄደው 43ኛው የቼዝ ኦሎምፒያድ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቼዝ ቡድን በግራንድ ማስተር ግሪቫስ  ስልጠና ማግኘቱን ገልጸዋል።

ስልጠናው ከሐምሌ 24 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ ቆይቷል።

ቼዝ በቤት ውስጥ ከሚካሄዱ የስፖርት ዓይነቶች አንዱ ሲሆን የሰው ልጅ አእምሮን የሚያሰፋ በመሆኑ በዓለም ላይ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ያዘወትሩታል።