ቀጥታ፡

ሦስቱ ሀገራት ወደ ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታታት ውጪ ምክር ቤቱ ሊያደርግ የሚችለው ነገር የለም... የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት

ሰኔ 25/2013(ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታታት ውጪ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ሊያደርግ የሚችለው ነገር አለመኖሩን አስታወቀ።

የጸጥታው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚሰበሰብ ተነግሯል።

ነገር ግን ምክር ቤቱ ሶስቱ ሀገራት ወደ ስምምነት ሊያደርስ ወደሚችል ድርድር እንዲመለሱ ከማድረግ ውጪ የጎላ ሚና እንደማይኖረው የምክር ቤቱ የወቅቱ ሰብሳቢ ኒኮላስ ዴ ሪቪዬር አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሆኑት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላስ ዴ ሪቪዬር ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በቀጣይ ሳምንት ምክር ቤቱ በግድቡ ዙሪያ ወይይት ሊያደርግ ይችላል።

ይሁን እንጂ ሶስቱን ሀገራት በመጥራት ስጋታቸውን እንዲገልጹና ከስምምነት ሊያደርሳቸው ወደሚችለው ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታታት ውጪ ሊያደርግ የሚችለው ነገር የለም ብለዋል።

ሰብሳቢው "ምክር ቤቱ ከዚያ የበለጠ ነገር ማድረግ ይችላል ብዬ አላስብም" ሲሉም ገልጸዋል ሲል ሬውተርስ ዘግቧል።

ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽ እና ሱዳን ጉዳዩን በተደጋጋሚ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት በመውሰድ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካ መፈታት አለበት የሚል ጽኑ አቋም እንደያዘች ቀጥላለች። በቅርቡ ለጸጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ መጠየቋ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም