ሰመራና ወልድያ ዪኒቨርሲቲዎች 7ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል

148

ሰመራ/ወልድያ/ባህርዳር ሰኔ 25/2013 (ኢዜአ) ሰመራና ወልድያ ዪኒቨርሲቲዎች ከ7 ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታወቁ።

የሰመራ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱራህማን ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ አዲስ የተመደቡለትን 2ሺህ 311 ተማሪዎች ነገና ከነገ በስትያ ይቀበላል።

ዮኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለመቀበል የመማሪያ ክፍሎች ፣ የመኝታ ቤት፣ የመመገቢያ አዳራሽን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን ዝግጁ ማድረጉን ተናግረዋል።

የመማር ማስተማር ሂደቱን በትምህርት ሚኒስቴር በወጣ የኮሮና መከላከል መመሪያ መሰረት ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከሚቀበላቸው ተማሪዎች ውስጥ 1ሺህ 361ዱ በተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም 950ዎቹ በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች የተደለደሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው አዲስ በተመደቡለት ተማሪዎች አጠቃላይ የቅበላ አቅሙ ከ8ሺህ በላይ እንደሚደርስ አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከአካባቢው አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ወልድያ ዩኒቨርስቲ 4 ሺህ 700 አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል።

የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሱልጣን መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው

ሰኔ 29 እና 30 2013 ዓም ባሉት ቀናት አዲስ ተማሪዎችን ይቀበላል።

ተማሪዎቹን ለመቀበል የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

ከሰኔ 22 ቀን 2013 አም ጀምሮ 5ሺህ 297 አዲስ ተማሪዎችን እየተቀበለ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነው።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች የተመደቡለትን አዲስ ተማሪዎች እየተቀበለ ነው።

ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር ከ41ሽህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም