በኢንዱስትሪ ፓርኮች እስካሁን ለ80 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩ ተገለጸ

3611

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25 2013ዓ.ም(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ተገንብተው ስራ በጀመሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እስካሁን ለ80 ሺህ ዜጎች ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ ጋዜጠኞችን የቦሌ ለሚ፣ የአዳማ እና የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የስራ እንቅስቃሴ አስጎብኝቷል።

በኮርፖሬሽኑ የትራንስፎርሜሽንና ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ ማሞ፤ ለጋዜጠኞቹ በሰጡት ማብራሪያ ስራ በጀመሩ ሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች እስካሁን ለ80 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።

በፓርኮቹ ከደመወዝ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን እንደሚታወጅ ተናግረዋል፡፡

በቀጣዮቹ 20 እና 30 ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቁጥር ከ100 በላይ በማድረስ የተሻለ የቢዝነስ ከባቢ ለመፍጠር መታቀዱንም ጠቅሰዋል።

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ትንሳኤ ይማም፤ ከፓርኩ ባለፉት 11 ወራት ምርቶችን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ 44 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው የጠቀሱት።

በፓርኩ አብዛኞቹ ባለሃብቶች በጨርቃ ጨርቅ መስክ መሰማራታቸውንና ከ18 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ሰራተኞች የሚገጥማቸውን ችግር ለማቃለል በፓርኩ ከሚሰሩ ባለሀብቶች ጋር በመተባበር የጋራ መኖሪያ ቤት እየተገነባ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም የፓርኮቹ ምርታማነታት እንዲጨምርና የሰራተኞች ፍልሰት እንዲቀንስ ያስችላል ብለዋል።

የአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ በበኩላቸው በፓርኩ የተገነቡ ሁሉም ሼዶች በባለሃብቶች መያዛቸውን ገልጸዋል።

በመንግስት ወጭ ከተገነቡት 19 ሺዶች መካከል ሁሉም በባለሃብቶች የተያዙ ሲሆን ስምንቱ ስራ መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።

በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥም 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሥራ እንዲገቡ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንና በኢንዱስትሪው ከሚሰሩ ባለሃብቶች ጋር በመነጋገር ለሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በፓርኩ እስካሁን ለ7 ሺህ ሰራተኞች የስራ እድል እንደተፈጠረ ጠቅሰው፤ ሼዶቹ ሙሉ በሙሉ ስራ ሲጀምሩ ከ20 እስከ 25 ሺህ ሰራተኞችን የመቅጠር አቅም ይኖራቸዋል ብለዋል።

ፓርኩ በ11 ወራት 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቻሉንም ጠቁመዋል።

እስካሁን ለ35 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም በ11 ወራት ከ114 ሚልዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የገለጹት ደግሞ የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ ናቸው።

በጥሬ ዕቃ ማስገባትና ምርቶችን በመላክ ሂደት ለአምራች ድርጅቶች ውስብስብ ያልሆነ የትራስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓልም ብለዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚሰሩ ሰራተኞች በበኩላቸው በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችም ለቤት ኪራይ ሳናስብ ገንዘባችንን ቆጥበን እንድንኖር ረድቶናል ብለዋል።