የተደረገላቸው አቀባበል ተረጋግተው እንዲማሩ እንደሚይግዛቸው በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ

67

አምቦ ፤ ሰኔ 24/2013 (ኢዜአ) የተደረገላቸው አቀባበል በአካባቢው ሰላም ላይ በመተማመን በተረጋጋ መንፈስ ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ እንደሚይግዛቸው በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

በዩንቨርሲቲው  ለተመደቡ አዲስ ተማሪዎች አቀባበል ተደረጎላቸዋል

ከአዲስ ገቢ ተማሪዎች መካከል ከአዲስ አበባ የመጣው ተማሪ ፋኑኤል ማቴዎስ ለኢዜአ እንዳለው፤  የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከአዲስ አበባ አውቶቡስ ተራ ጀምሮ በመቀበል ያለምንም ችግር ወደ ግቢ መግባት ችለዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶችና ሌላውም የአምቦ ከተማ ማህበረሰብ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራርና ነበር ተማሪዎች ያደረጉላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል እንዳስደሰተው ገልጿል፡፡

የትምህርት ጊዜው በኮሮና ምክንያት  ቢራዘምም ትምህርት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ጠንክሮ በመማር የባከነውን ጊዜ በማካካስ  ውጤታማ ለመሆን እንደሚጥር ተናግሯል፡፡

ከደቡብ ክልል የመጣው ሳሙኤል ዋንታሞ በበኩሉ፤ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆኑን ገልፆ በቀጣይም ራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅና ከማንኛውም ህገ- ወጥ ድርጊት በመቆጠብ ለትምህርት ብቻ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ለመሆን እጥራለሁ ብሏል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ነባር ተማሪዎች ወደዩኒቨርሲቲው ስትገባ ጀምሮ ባደረጉላት አቀባበል መደሰቷን የተናገረችው ደግሞ ከኦሮሚያ የመጣችው ተማሪ ባዩሽ አለማየሁ ናት።

ነባር ተማሪዎች ባደረጉላት አቀባበል በቀላሉ የምትፈልገውን አገልግሎቶችን በማግኘቷ ለትምህርቷ ትኩረት በመስጠት ዓላማዋን ለማሳካት በርትታ እንደምትሰራ ገልጻለች ።

ተማሪዎቹ በማህበረሰቡ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በአካባቢው ሰላም ላይ  በመተማመን በተረጋጋ መንፈስ  ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ እንዳመቻቻቸው ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ባይሳ ለታ በበኩላቸ፤ ዘንድሮ  ወደ ዩኒቨርስቲው 3 ሺህ 524 አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተመድበዋል ብለዋል።

ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ በመንገድ ላይ እንግልትና መጉላላት እንዳይደርስባቸው አዲስ አበባና ነቀምቴ ድረስ ተሽከርካሪ በመመደብ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

ልጆቻችሁን ወደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ የላካችሁ ወላጆችም ልጆቻችሁን በአደራ ተቀብለናል፤ ከዚህ በኋላ የኛ ልጆች ስለሆኑ ስጋት ሊገባችሁ አይገባም” ብለዋል።

አስፈላጊው  ግብአቶችና አገልግሎቶች መሟለታቸውን የጠቆሙት ዶክተር ባይሳ፣ ተማሪዎች የመጡበትን የትምህርት ዓላማ ለማሳካት ሰላምን በማስቀደም ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ሲደርሱ እንዳይደናገሩ ቀደም ብሎ የመኝታ ክፍሎች ዝግጅት መከናወኑን የገለጸው ደግሞ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዘዳንት ተማሪ ኦሊ በዳዳ ነው፡፡

ተማሪዎች ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎች በመቆጠብ በትምሀርታቸው ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በአቀባበሉ ስነ-ስርዓት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም  የአካባቢው ማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

አምቦ ዩኒቨርሲቲ 30ሺህ የሚደርሱ አዲስና ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝ  ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም