በኢትዮጵያ በቀጣይ አስር ዓመታት ሙቀት አማቂ ጋዝን ለመቆጣጠር 316 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

60

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቀጣይ አስር ዓመታት ሙቀት አማቂ ጋዝን ለመቆጣጠር 316 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የአካባቢ፣ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ መቀነሻ እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።

የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ፤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት  የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግሩ የሰፋና አፋጣኝ መፍትሔን የሚሻ ሆኗል።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ አገራት ተጽእኖው የከፋ ከመሆኑ ባሻገር ለአገር እድገት በሚደረገውን እንቅስቃሴ ላይ ማነቆ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት ላይ አባል ከሆኑና ስምምነት ከፈረሙ አገራት መካከል እንደምትገኝ አንስተዋል።

ኢትዮጵያም ችግሩን ለመፍታት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር የአምስት ዓመት የእቅድ ክለሳ ስራ እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዛት እየተከሰተ ያለው ተፈጥሯዊ አደጋ፣ የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር ለእቅዱ ክለሳ ዋና ዋና ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዚህም በራስ አቅም እስከ 14 በመቶ  ሙቀት አማቂ ጋዝን ለመቀነስ ያቀደች ሲሆን በዓለም አቀፍ ተባባሪ አካላት እስከ 68 በመቶ ለመቀነስ እቅድ ተይዟል ብለዋል።

ለዚህም በሁሉም ሴክተሮች የሚሰሩ ስራዎችን በማካተት በአስር አመት ውስጥ 316 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።

እቅዱን ለማሳካት በጀት የማፈላለግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢኒሼቲቭ ሪጅናል ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ጀምበር፤ አገራት አማቂ የጋዝ ልቀትን 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሼልሲየስ ለማድረስ መስራት አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢኒስቲትዩት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ገመዶ ዳሌ እንዳሉት የተቀመጡ እቅዶች ግቦች ውጤታ እንዲሆኑ ማህበረሰቡን፣ የመገናኛ ብዙሃንንና የባለድርሻ አላትን ግንዛቤ ማጎልበት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ተቋማዊ አቅም መገንባትና የፋይናንሰ አጠቃቀምን በአግባቡና በወቅቱ እንዲሆን ወጥነት ያለው አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም