በክረምቱ ከ38 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ ስራ ለማከናወን ተዘጋጅተናል- ሚኒስቴሩ

3389

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው ክረምት ከ38 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ለማከናወን መዘጋጀቱን የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ እንደገለጹት፤

በዘንድሮው የበጎፈቃድ አገልግሎት ከ38 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 13 የተለያዩ የበጎፈቃድ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በቡታጅራ ከተማ ነገ 500 ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የችግኝ ተከላና የደም ልገሳ መርሃ ግብር የሚከናወን መሆኑን በሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ ገልጸዋል።

በቀጣይም በመርሃ ግብሩ ለአረጋውያንና አቅመ-ደካሞች  ቤት በማደስ፣ ትምህርት ቤቶችን በመጠገንና የማጠናከሪያ ትምህርቶችን በመስጠት፣ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ይከናወናል ብለዋል።

ለክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 16 ሚሊየን ወጣቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቅሰው በዚህም ከ10 ቢሊየን ብር  በላይ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አብራርተዋል፡፡

ባለፈው ክረምት እና በጋ 23 ሚሊየን የሚደርሱ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ ከ66 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ መስጠታቸውንና በዚህም የ8 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ወጣት ኤርሚያስ ማተቤሳ በበኩሉ፤ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ሚሊየን በላይ መጽሐፎችን ከበጎፈቃደኞች ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግሯል፡፡

የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር የአረጋውያንና አቅመ-ደካሞችን መኖሪያ ቤት ለማደስ ፌዴሬሽኑ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አብራርቷል፡፡