ከሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ስደተኞቸን መልሶ ለማቋቋም ከመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

229

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም ከመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ።

የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ከቅረብ ጊዜ ወዲህ ከሳውዲ አረቢያ ለሚገቡ ስደተኞች ፈጣን መፍትሄ ስለሚያስፈልጋቸው ልዩ እቅድ በማወጣት የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

አቶ ንጉሱ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ዜጎች ላይ ለተከሰተው ችግር ፈጣን መፍትሄ ለመስጠት ልዩ እቅድ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ከስደት ለተመለሱት ዜጎች በፍጥነት የስራ ዕድል ሊመቻች የሚቻልበተን ሁኔታ በመቅረፅ፣ በማቀድ እንዲሁም ሃብት በማፈላለግ እና በሥራ ስምሪት ረገድ የተለያዩ ተግበራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ተግባር የተቋማትን ትብብርና ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

ለዚህም ኮሚሽኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራን መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከፌዴራል እስከ ክልል ባሉ የመንግስት ተቋማት መዋቅር ተዘርግቶ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከስደት በመመለስ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ከአየር መንገድ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እየተደረገ ነው።

ተመላሾቹ ወደ አገር ከገቡ በኋላ ለማቋቋም በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ ግብረ ሃይል ከተለያዩ ተቋማት መቋቋሙን ተናግረዋል።

በየአካባቢያቸውም ሄደው ባላቸው የትምህርት ደረጃ ልምድ እና የቤተሰብ ሁኔታ ታይቶ የስራ ዕድል እየተፈጠረላቸው መሆኑ ገልፀዋል።

ስደተኞቹ በእስር ቤት ብዙ ስቃይና መከራ የደረሰባቸው መሆኑን ያስታወሱት ወይዘሮ አየለች፤ በስነ ልቦና ባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ወደ አካባቢያቸው እንዲሄድ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እያደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግስት ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን በአንድ ሳምንት ውስጥ በ35 በረራዎች 10 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ከሳውዲ ወደ አገራቸው መመለሳቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም