የዳውሮ ዞን ወጣቶች ሀገራዊ ለውጡን በመደገፍ የልማት ስራ አከናወኑ

80
ሶዶ ሀምሌ 29/2010 የዳውሮ ዞን ወጣቶች በመንግስት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ የመንገድ ልማት ስራ አከናወኑ፡፡ ወጣቶቹ ዛሬ ያከናወኑት የመንገድ ልማት ስራ ለረጅም ዓመታት ይሰራል ተብሎ ሲጓተት የቆየው የተርጫ ወልዴሃኒ ዱርጊ ዱራሜ መንገድ ነው፡፡ መንግስት የአከባቢውን ወጣቶች የልማት ተነሳሽነትና አዋጪነቱን ተመልክቶ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡ ከሁሉም የዞኑ አካባቢዎች የተወጣጡ ወጣቶች የልማት ስራውን በራሳቸው ተነሳሽነት እንዳከናወኑና እንደሚቀጥሉበት በሰጡት አስተያየት  አረጋግጠዋል፡፡ የወጣቶች አስተባባሪ መምህር ብርሃኑ ዱባለ በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ በተፈጠረው የመደመርና ይቅርታ መርህ በመደገፍ የጀመረውን ሀገራዊ  የለውጥ ጉዞ እንዲቀጠል የድርሻቸውን ለመወጣት መነሳሳታቸውን ተናግረዋል ከታርጫ ወልደሃኒ ዱርጊ አድርጎ እስከ ኦሞ ወንዝ ድረስ ያለውን ከ35 ኪሎ ሜትር በላይ ለማጠናቀቅ ወጣቱ እንደወሰነ ጠቅሰው በእስካሁኑ ሂደትም 5 ኪሎ ሜትር መስራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በየሳምንቱ በመገናኘት ለማጠናቀቅ ተዘጋጅተዋል፡፡ በተለይም የዳውሮ አካባቢ ተገቢ የሆነ የመንገድ መሰረተ ልማት የተመቻቻለት ባለመሆኑ  ሲቸገርና የታርጫ ወልዴሃኒ ዱርጊ ዱራሜ መንገድ በተደጋጋሚ ይሰራል ተብሎ ቃል ተገብቶ ሲጓተት ቆይቷል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው መንገድ ግልጌል ግቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሲሰራ ውሃ በመሙላቱ ምክንያት እንዲዘጋ በመደረጉ የዳውሮ ህዝብ ለዘመናት በጎራባችነት ከሚኖረው የካምባታ ጣምባሮ ፣ሃዲያና ኦሮሚያ ጋር እንዲቆራረጥ ምክንያት መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በመደረጉ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ቅሬታ ማሳደሩን ጠቅሰው ወደ ሶዶ ተለዋጭ የተሰራው መንገድ ኪሎ ሜትሩ በመጨመሩ ለእንግልት መዳረጉን አውስተዋል፡፡ ከገና ቦሳ ወረዳ የመጣው ወጣት ሺመልስ ታደሰ በሃገሪቱ ላይ የተፈጠረው የለውጥ እንቅስቃሴ ያለማንም አነሳሽነት የመንገድ ልማት ስራውን ማከናወናቸውን ገልጿል፡፡ በተለይም ለዚህ መንገድ ስራ ቅድሚያ ሊንሰጥ የቻልነው የአካባቢዉ ህብረተሰብ የመንገድ መሰረተ ልማት እጦት የተነሳ ለተለያዩ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጡን አመልክቷል፡፡ ወጣት ሺመልስ እንዳለው  በራሳቸው ተነሳሽነት በእጅቸው ሰርተን እናጠናቅቀዋለን ብለው የጀመሩት ሰሚ በማጣታቸው ምክንያት ከጠባቂነት በመውጣት ሃገራዊ ለውጡን መደገፋቸውን በተግባር በማሳየት  የመንግስትን ምላሽ ለማፋጠን መሆኑን ነው፡፡ በገና ቦሳ ወረዳ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ቄሲስ መኮንን መለሰ ለረጅም ዓመታት ጥያቄ ከመሆንም ባለፈ የመንግስት አካላት ተገቢ ምላሽ ባለመስጠታቸው ከመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አንዱ ሆኖ መቆየቱን አስታወሰዋል፡፡ ወጣቶቹ የጀመሩት ተግባር እንደሚደግፉና መንግስትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ወጣቶቹ በራሳቸው ተነሽነት የታርጫ ወልዴሃኒ ዱርጊ ዱራሜ የመንገድ ልማት ስራ ለመስራት መሰማራታቸው የሚበረታታና መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዳውሮ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደስታ ናቸው፡፡ ከወጣቶቹ ጋር በመደመር የመንገድ ልማቱን ለማጠናቀቅ ህዝብን ለማስተባበርና ጥናት ላይ የተመሰረተ በቂ መረጃ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ የዞኑ አስተዳደር እንደሚሰራ አቶ ዳዊት አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም