ምርትን ከብክነት ለመታደግ በፀረ-ተባይ ኬሚካል የታከመ ከረጢት መጠቀም እንደሚገባ ተመለከተ

133
አዳማ ሀምሌ 29/2010 ምርት በክምችትና አያያዝ  ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን ብክነትና የጥራት መጓደል ለመቀነስ በፀረ-ተባይ ኬሚካል የታከመ ከረጢት መጠቀም እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ በፀረ-ተባይ ኬሚካል የታከመ ከረጢት አስፈላጊነትና አጠቃቀም ለማስተዋወቅ ለኀብረት ሥራ ማህበራትና ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ የምክክር መድረክ  በአዳማ ከተማ ተካሂዷል። የፌዴራል ኀብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በዚህ ወቅት እንደገለጹት ኀብረት ስራ ማህበራት በዓመት በአማካኝ ከ13 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት ያገበያያሉ ። "የግብይት ሂደት ጋር ተያይዞ ቢያንስ ከ13 ሚሊዮን በላይ ከረጢቶችን ይጠቀማሉ" ብለዋል። ማህበራቱ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርባቸው ምርትቶች በክምችትና በአያያዝ ወቅት በተባይ በመጠቃት ለብክነትና ለጥራት ጉድለት እንደሚዳረጉ ጠቁመዋል። በተጨማሪም በተለያዩ ኬሚካሎች ብክለት ስለሚደርስባቸው በግብይቱ ሂደት ተግዳሮት እያጋጠመ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኤጀንሲው የችግሩን ታሳቢነት በመገንዘብ "እድሜዓለም እጅጉ ቢዝነስ ግሩፕ " ከተባለው ድርጅት ጋር በመተባበር የፀረ-ተባይ ኬሚካል የታከመ ከረጢት አጠቃቀም ለህብረት ስራ ማህበራት ለማስተዋወቅ መድረኩን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል። ከረጢቱ የምርት ብክነትን በመከላከል ጥራትን ለማስጠበቅ አይነተኛ አማራጭ በመሆኑ ህብረት ስራ ማህበራት በስፋት ቢጠቀሙና ለአባሎቻቸውም ቢያሰራጩ ችግሩን ማስወገድ እንደሚቻል አመላክተዋል። የእድሜአለም እጅጉ አስመጪና ላኪ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እድሜዓለም እጅጉ በበኩላቸው ድርጅቱ የጥራጥሬ፣ቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የበርካታ ዓመታት ልምድ እንዳለው ገልጸዋል። "ይሁንና በድህረ ምርት ወቅት ከክምችትና አያያዝ ጋር ተያይዞ ከተባይና ነፍሳት እንዲሁም በኬሚካል ንክኪ በሚያጋጥም የምርት ብክነትና የጥራት መጓደል ሀገሪቱ ከዘርፉ በምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ነው" ብለዋል። ተቋማቸው ችግሩን ለመፍታት በፀረ-ተባይ ኬሚካል የታከመ ከረጢት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ከረጢቱ በሀገሪቱ በሚመለከተው አካል ውጤታማነቱ ከተረጋገጠ በኋላ በግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር መመዝገቡን ያመለከቱት ስራ አስኪያጁ በቀጣዩ ወር ም መጨረሻ ላይ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያሳገቡ  አመላክተዋል። የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እያሱ አብርሃ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂውን አስፈላጊነትና ለአርሶ አደሩ የሚሰጠውን ጠቀሜታ በመረዳት ምርቱ ሀገር ውስጥ እንዲገባ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አረጋግጠዋል። "ከረጢቱ ለአርሶ አደሮችና ለነጋዴዎች የምርት ብክነትና ጥራት መጓደል ችግሮችን በመከላከል እስከ ሁለት ዓመት የሚዘልቅ አስተማማኝ  የማጠራቀሚያ አገልግሎት የመስጠት አቅም አለው"ብለዋል። የኢትዮጵያ የቅባት፣ጥራጥሬና ቅመማ ቅመም ላኪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ዮሐንስ የማህበሩ አባላት በአያያዝ ጉድለት በተባይ የተጠቃ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ላለፉት ሶስት ዓመታት ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል። ከረጢቱ ከአርሶ አደሩ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለመረከብ ስለሚያስችል የውጭ ግብይቱን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡ ትናንት የምክክር መድረክ ከሁሉም ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኀብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ስራ አስኪያጆች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም