በኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ከተዘሩ ሳይበሰብሱ ለዓመታት ምርት የሚሰጡ የጤፍና የማሽላ ዝርያዎች በምርምር ተገኙ -ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

3964

አዲስ አበባ ግንቦት7/2010 ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ከተዘሩ በኋላ ሳይበሰብሱ ለዓመታት ምርት መስጠት የሚችሉ የጤፍና የማሽላ ዝርያዎች በምርምር ማግኘቷን አስታወቀች።

የምርምር ግኝቶቹ  ”የዓለምን የሰብል ልማት ታሪክ ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው” ተብሏል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂኔር ጌታሁን መኩሪያ የመስሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖረት ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አገሪቷ የጀመረችውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ በርካታ የምርምር ስራዎች ተከናውነዋል፤ ወደ ተግባር የመተርጎም ሥራም ተጀምሯል።

ከነዚህ የምርምር ውጤቶች መካከልም አንድ ጊዜ ከተዘራ ለተከታታይ 20 ዓመታት ምርት የሚሰጥ የማሽላ እና ለ10 ዓመታት ፍሬ የሚያፈራ የጤፍ ዝርያዎች ይጠቀሳሉ ብለዋል።  እነዚህ የምርምር ግኝቶች ”የዓለምን የሰብል ልማት ታሪክ ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው” ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በምርምር የተገኙትን ዘሮች የማባዛት ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ የማባዛት ሥራው እንደተጠናቀቀ በመጪው በጀት ዓመት በአገሪቷ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ይሰራጫል ብለዋል።

በሌላ በኩል በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሳይንስ ትምህርትን በኮምፒዩተር ሶፍትዌር ”ቨርቹዋል ላቦራቶሪ” የታገዘ ለማድረግ የሚያስችል ሥራም በመከናወን ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ይኸው የማስተማሪያ ስርዓት በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ቦሌ፣ ጥቁር አንበሳና ዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙከራ እየተደረገበት መሆኑንም ገልፀዋል።

የሶፍት ዌር ቴክኖሎጂው የባዮሎጂ፣ ኬሚሰትሪ፣ ፊዚክስና ሂሳብ ትምህርት አሰጣጥን በቁሳዊ ቤተ ሙከራዎች መደገፍ ከሚችለው በተሻለ መልኩ ተግባራዊ ሙከራዎችን ማካሄድና የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ሙከራው ሲጠናቀቅም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአገሪቷ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፋ ይደረጋል፤ አጠቃቀሙን በተመለከተም ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።