ጅማ ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን የቡና ችግኝ በመትከል ጀመረ

104

ጅማ፣ ሰኔ 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ የቡና ችግኝ ተከላ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በዩኒቨርሲቲው በግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ስር በሚገኘው ኢላዳሌ እርሻ ጣቢያ ዛሬ በይፋ ጀመረ።

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ለመማር ማስተማር፣ ለምርምር፣ ለማህበረሰብ አገልግሎትና ለገቢ ማመንጫ እንዲውል በማሰብ የሚካሄድ ነው።

በዘንድሮ ክረምት 25 ሺህ የቡና ችግኞች ዩኒቨርሲቲው እንደሚተክል ተናግረው፤ "ችግኞችን ስንተክል በሳይንሳዊ መንገድ መሆን አለበት" ብለዋል።

የተተከሉ ችግኞችን ለመንከባከብና ለመጠበቅ ሁሉም በሃላፊነት መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

የአረንጓዴ አሻራው በየአመቱ የሚቀጥል በመሆኑ ፍራፍሬዎችንና ቡናን ጨምሮ ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የችግኝ ዓይነቶች እየተተከሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

መርሃ-ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ “ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” የሚል ጥሪ አካል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ዲን ዶክተር ፍቃዱ ምትኩ መርሃ ግብሩ ምርምር፣ መማር ማስተማርና ማህበረሰብ አገልግሎትን ለማስቀጠል እንደሚረዳ ጠቅሰዋል።

በተለይም ዩኒቨርሲው የራሱን ገቢ በማመንጨት ራሱን እንዲችል ለማድረግ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። የተተከሉት የቡና ችግኞች ምርት መስጠት ሲጀምሩ በዩኒቨርሲቲው አርማ ለገበያ እንዲቀርቡ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም