የኢትዮጵያን መፃኢ ብልጽግና በእውቀትና በጥበብ የሚመሩ አመራሮችን ለማፍራት በትኩረት ይሰራል ... ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 19/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያን መፃኢ ብልጽግና በእውቀትና በጥበብ የሚመሩ አመራሮች ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባውን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የስልጠና ማዕከል መርቀው ሲከፍቱ ነው፡፡

ለማዕከሉ ግንባታ ከወጣው ወጪ 722 ሚሊዮን ብር በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን፤ ቀሪው ከቻይና መንግስት የተገኘ ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካዳሚው ለመንግስትና ለቢዝነስ አመራር አባላት እንዲሁም ለተተኪ ወጣቶች "የእውቀት ብርሃን የሚያፈልቅ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

"የኢትዮጵያና የአፍሪካ ችግር የእውቀት ብርሃን ማጣት ነው" ያሉት ዶክተር አቢይ፤ ይህ ደግሞ "እርስ በእርስ እንድንጋጭና አንዳችን ከሌላችን ጎን እንዳንቆም አድርጎናል" ብለዋል፡፡

የውጭ አገራት አፍሪካዊያንን የሚመዝኑት ለእነርሱ በተመቸ መንግስት እንጂ በዴሞክራሲና በልማት አለመሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገራቸውን ለማልማት ቆርጠው በተነሱ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የውጭ ጫና መኖሩንም አንስተዋል።

አፍሪካዊያን ይህን ችግር ማለፍ የሚችሉት በእውቀትና ጥበብ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር አካዳሚው ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካዊያን ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

አካዳሚው ከዚህ ቀደም የመንግስት ካድሬዎችን ብቻ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ጽንሰ ሃሳብ ሲያሰለጥን መቆየቱን አስታውሰዋል።

አካዳሚው ባለፉት ሁለት ዓመታት ይሰጥ የነበረውን ስልጠና አቋርጦ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ተሻገሪ በሆነ መልኩ እንዲደራጅ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት።

በመሆኑም አካዳሚው ያደረገው የስያሜ ለውጥ ይዞት የተነሳውን ራዕይና አዲስ አደረጃጀት የሚያሳይ እንጂ ከዚህ በፊት ይጠራበት የነበረውን ስም ከመቀየር ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም ብለዋል።

አካዳሚው ከመንግስት ኃላፊዎች በተጨማሪ ለግል ተቋማት አመራሮች፣ ለዲፕሎማቶች፣ ለጸጥታና ሌሎች ተቋማት አመራሮች ስልጠና እንዲሰጥ ተደርጎ መደራጀቱንም ጠቁመዋል።

አካዳሚው በኢትዮጵያ ከሚገኙት የትምህርት ተቋማት በተለየ ዘመናዊ ሆኖ መገንባቱንም አክለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አካዳሚው በብዙዎች ዘንድ ያለውን አለማወቅ፣ በጥበብ አለመሞላት ደረጃ በደረጃ የሚቀርፍና የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ አጋዥ ሚና የሚጫወት ነው።

ሁሉም የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሌሎችም በአካዳሚው ገብተው በመማር የአገሪቷን ብልጽግና እውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ጃው ጂዩዋን የአካዳሚው ግንባታ  በኢትዮጵያና  ቻይና መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የአመራር ስልጠና ከአገር ልማት ጋር እንደሚያያዝም ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

የአካዳሚው ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ በበኩላቸው አካዳሚውን በአንድ ዓመት ከመንፈቅ ገንብቶ ማጠናቀቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ይህም ያለ ጊዜና ሃብት ብክነት ግዙፍ ስራዎችን መከወን እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ነው ያብራሩት።

አካዳሚው 600 ሰው የሚይዝ ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽ፣ 500 ሰው በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ የመመገቢያ አዳራሽ፣ የሰልጣኞች መኝታ ክፍሎች፣ ጅምናዚየም፣ የገበያ አዳራሽና ሌሎች ክፍሎች እንዳሉት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር በመሆን በአካዳሚው ቅጥር ግቢ ችግኝ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም