በመጠለያ ውስጥ የቆዩ ዜጎችን ከማኅበረሰቡ ጋር ለማገናኘት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ስራ ይጠይቃል - ብ/ጀኔራል አለማየሁ ወልዴ

99

ሰኔ 19/2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን ከቀያቸው ተፈናቅለው የቆዩ ዜጎች ዳግም ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲገናኙ ሰፊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ስራ እንደሚጠይቅ የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ አሳሰቡ።

በዞኑ ቡለን ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት የሚፈታ የእርቀ ሠላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

በኮንፈረንሱ የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች፣ የክልል የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ባከናወናቸው ተግባራት አንጻራዊ ሠላም በመስፈኑ በግጭቱ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ ዜጎችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራ እየሰራ ይገኛል።

ጎን ለጎንም በተለያዩ ወረዳዎች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ የእርቀ ሠላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ እርቀ ሠላም ከወረደ በኋላ ከቀያቸው የተፈናሉ ዜጎችን ለማገናኘት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የወረዳና የክልል የስራ ኃላፊዎችም አጠቃላይ ስምሪቱን የመስጠት ስራዎችን ማከናወን እንሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሠላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ "ከሞት፣ ከመፈናቀልና ጥላቻ የሚገኝ አንዳች መልካም ነገር የለምና እውነተኛ እርቅ በመላበስ የተበደለውን ወገናችንን መካስ ይገባል" ብለዋል።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ የሠላምን ዋጋ በመረዳት ተቋርጦ የነበረውን ማኅበራዊ መስተጋብር ማሰቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የቀደመ አብሮነትና አንድነቱን በማጠናከር ለጋራ ሠላምና እድገት በትብብር መስራት እንደሚኖርበት በሠላም ኮንፈረንሱ የተሳተፉ የቡለን ወረዳ ነዋሪዎች አንስተዋል።

በወረዳው ያሉ የልማት አማራጮች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሁሉም ለሠላም ዘብ መቆም እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

ጫካ ገብተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ተወካዮች ለደረሰው ጥፋት ይቅርታ በመጠየቅ በቀጣይ ያስከፉነውን ኅብረተሰብ ለመካስ ዝግጁ ነን ብለዋል።

በእርቀ ሠላም መርሃ ግብሩ ላይ ለሂደቱ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋናና እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ጫካ ገብተው የነበሩ ታጣቂዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮችም ባሕላዊ የእርቀ ሠላም ሥነ-ስርዓት አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም