የክልሉ መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳው ነው - የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር

85
ሀዋሳ ሀምሌ 28/2010 የክልሉ መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ፡፡ ህዝቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም የክልሉ መንግስት ያስተላለፈውን ጥሪ ተግባራዊ እያደረገ በመሆኑም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥ የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ በተቀናጀ መንገድ ህገ ወጥነትን ለመታገል እያሳየ ያለውን አቋም አጠናክሮ መጠቀል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ እንደ አቶ ሚሊዮን ገለፃ የክልሉ መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እየሰራ ነው፡፡ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶች በአሁኑ ወቅት መርገባቸውን የተናገሩት አቶ ሚሊዮን ወጣቶች የሚያነሱትን የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በሰከነ ስሜት መጠየቅ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ "ህዝብ ደህንነቱ የሚጠበቅበት፣ በሰላም ወጥቶ የሚገባበትና የእለት እንቅስቃሴው የማይደናቀፍበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ለፀጥታ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመዋቅር ጥያቄዎች በተረጋጋና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ጠብቆ ማቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ በቅርቡ በጋሞ ጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ተከስቶ የነበረው ግጭት መቆሙን የገለጹት አቶ ሚሊዮን የጎፋ ህዝቦች ያቀረቡት የዞን መዋቅር ጥያቄ ጥናት እየተደረገበት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥበት አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የመንግስት አሰራርን ህግን ባልተከተለ መልኩ መጣስ ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በህዝቡ ውስጥ ያለው የለውጥ ስሜት በጥንቃቄ መምራት የሚገባው በስልጣን ላይ ያለው ደኢህዴን/ኢህአዴግም ለውጡን መምራት የሚያስችል ቁመና ሊኖረው እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶች እንዳሉ ሆነው እርካታን መፍጠር ያልቻሉ መሰረታዊ ጉዳዮች በመኖራቸው የፖሊቲካ ምህደሩን ማስፋት እንደሚያስፈልግም አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የፖሊቲካ አስተሳሰቦችና ፍላጎቶች በአንድ ላይ መስተናገድ መጀመራቸው እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወሰድ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡ የክልሉ አመራሮች ከየትኛውም ጊዜ በላይ አቅማቸውን በማጠናከር ህብረተሰቡን የማስተባበር ስራ መስራትና  ለውጡን በትክክል በመገንዘብ የማይተካ ሚና መጫወት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በክልሉ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸውና ቤታቸው የመመለስ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡ በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች አማሮ፣ ቡርጅና ጌዲኦ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታትም ከፌዴራልና ከአሮሚያ መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም