በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ህገ-ወጥ ሰፋሪዎች እያደረሱ ያለውን ችግር ለመከላከል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

129
ጋምቤላ ሀምሌ 28/2010 በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ህገ-ወጥ ሰፋሪዎች እያደረሱ ያለውን ችግር ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ጥሪ አቀረበ። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በፓርኩ ብዝሃ ህይወት ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከል የጥበቃ ቤቶችን የመገንባትና የሰው ኃይል አደረጃጀቱን እያጠናከረ መሆኑንም ገልጿል። በባለስልጣኑ የፓርኮችና መጠለያዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት የቀጠና አስተባባሪ አቶ መኳንንት ክንፈ እንደገለጹት በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ድንብር ዘለል የፈላታ አርብቶ አደሮችና ህገ-ወጥ ሰፋሪዎች በፓርኩ ብዝሃ ህይወት ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው። በተለይ የፈላታ ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮች ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የቀንድ ከብት ይዘው ወደ ፓርኩ ይዞታ በመግባት በብዝሃ ህይወት ሀብቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ የእንስሳት ሀብቱ እንዲሰደዱ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን ለመከላከል የጥበቃ ቦታዎችን የማስፋት፣ የጥበቃ ቤቶችን የመገንባትና የሰው ኃይል አደረጃጀቱን የማጠናከር ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ችግሩን የመከላከሉ ሥራ ያለ ህብረተሰቡና የክልሉ ፀጥታ አካላት ተሳትፎ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችልም ጠቁመዋል። በመሆኑም ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮችና ህገ ወጥ ሰፋሪዎች በፓርኩ ላይ እያደረሱ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የህዝቡና የክልሉ የጸጥታ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠይቀዋል። የፓርኩ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሄኖክ ታምሩ በበኩላቸው ፓርኩ የተለያዩ ተግዳሮቶች በከፍተኛ ሁኔታ እያገጠሙት መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም የፈላታ አርብቶ አደሮች በየዓመቱ ከታህሳስ ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በርካታ የቀንድ ከብቶቻቸውን ወደ ፓርኩ ይዘው በመግባት ከፍተኛ ውድመት እያደረሱ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል ከሚመለከታቸው የክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። "ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ የፈላታ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ፓርኩ በመግባታቸው ምክንያት ቀደም ሲል የነበሩት የዱር እንስሳት ሸሽተዋል'' ያሉት ደግሞ የፓርኩ የጥበቃ ባለሙያ አቶ ኡቻን ቦት ናቸው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኪዊች ውዊ እንደተናገሩት ድንበር ዘለል የፈላታ አርብቶ አደሮችና ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ህገ ወጥ ሰፋሪዎች በፓርኩ ብዝሀ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ህገ ወጥ ሰፋሪዎቹ የክልሉን አርብቶ አደሮች ግጦሽ የመሻማትና ድንበር ዘለል የቀንድ ከብት በሽታ ሊያመጡ ይችላል የሚል ስጋት ጭምር እንዳለም ተናግረዋል። በመሆኑም የክልሉ መንግሰት ድንበር ዘለል ህገ - ወጥ ሰፋሪዎችን በ2011 በጀት ዓመት ለመካለካል በዕቅድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የፓርኩን የጥበቃ ቦታዎች ለማስፋትና ለጥበቃ ሠራተኞች ምቹ የሥራ ቦታን ለመፍጠር ያስገነባቸው ቤቶች በባለድረሻ አካላት ተጎብኝተዋል። የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ 4ሺህ 575 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡም 69 ዓይነት የአጥቢ እንስሳት፣ 327 የተለያዩ አዕዋፋትና 492 የእጽዋት ዝርያዎች እንደሚገኙበት ከፓርኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም