በዘንድሮው የምርጫ ሂደት በ97 የነበረው የምርጫ ውጤት መቀልበስ ይኖራል የሚል ጥርጣሬ የለኝም-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

48

አዲስ አበባ፣ ሰኔ14/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው የምርጫ ሂደት በ97 የነበረው የምርጫ ውጤት መቀልበስ ይኖራል የሚል ጥርጣሬ የለኝም ሲሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በአዲስ አበባ በምርጫ ክልል 23 ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ድምፅ ከሰጡ በኋላ በሰጡት መግለጫም የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ከዚህ በፊት እንደነበረው ውጤቱ የሚቀለበስበት እንደማይሆን አምናለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

በዘንድሮው የምርጫ ሂደት በ97 የነበረው የምርጫ ውጤት መቀልበስ ይኖራል የሚል ጥርጣሬም የለኝም ብለዋል።

ምርጫውን ለአሜሪካም ሆነ ለሌሎች አገሮች ብለን የምናደርገው ሳይሆን ለራሳችን ህልውና የምናከናውነው ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግሥት ለመመስረት ከዚህ የተሻለ አማራጭ የለም ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ መቀጠል አለበት ብለዋል።

እርሳቸው ድምፅ በሰጡበት የምርጨጫ ጣቢያ በጥሩ ሁኔታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ደግሞ በጉለሌ ምርጫ ጣቢያ 10/11 ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን የዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት እንደሚሆን ኢዜማ ተስፋ አለው ብለዋል።


ምርጫ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ የሚደረግ የመንግስት መምረጫ መንገድ ነውና ይህንን ህዝቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።


ትላንት እና ዛሬ የነበረው የምርጫ ድባብ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ ገልጸው ይህም በዚሁ ሁኔታ እንዲያልቅ እንፈልጋለን ብለዋል።


ኢትዮጵያ የአፍሪካም የአለምም ምሳሌ የምትሆንባቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም በዚህም ምርጫ አረአያነታችንን ለአለም ማሳየት አለብን ነው ያሉት።

የኢዜማው ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጊ በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 12 እና13 ድምጽ ሰጥተዋል።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለመምረጥ በወጡበት ሰአት የተረጋጋና ሰላማዊ እንደነበር ተናግረዋል።

ምርጫ ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ በመሆኑ ዜጎች እድሉን ተጠቅመው የሚበጃቸውን ፓርቲ ካለማንም አስገዳጅ ሊመርጡ ይገባል ብለዋል።

መራጩ በጎ ያልሆኑ ወሬዎችን ታግሎ የወደፊቱን የሃገሪቷን መጻኢ እድል ለመወሰን ምርጫ ሰላማዊ ትግል በመሆኑ መራጮች የሚፈልገውን ፓርቲ መምረጥ እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም