የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሰላማዊ መሆኑን መራጮችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ

62

ሃዋሳ፤ ሰኔ 14/ 2013(ኢዜአ) በሲዳማ በንሳ ምርጫ ክልል ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ የቀጠለው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሰላማዊ መሆኑን በአካባቢው መራጮችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ፡፡

በምርጫ ክልሉ ኢዜአ ተዘዋዉሮ ያነጋገራቸው መራጮች ከማለዳ 11 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ ለመስጠት በቦታው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዳዬ 01 አዳራሽ አንድ ምርጫ ጣቢያ ድምጽ ሰጥተው ሲወጡ የነበሩት አቶ ዳኒሶ ዳንጊሶ እንዳሉት፤ በዕለቱ የመጀመሪያው መራጭ እንደሆኑና የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱም ሰላማዊ ነው።

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱም ሆነ የምርጫ ቁሳቁሶች ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻሉና የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት በተገቢው የሚገልጹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ ድምጽ ሰጪ ወይዘሮ ዝናሽ አዳነ በበኩላቸው፤ከማለዳ 11 ሰዓት ላይ ድምጽ ለመስጠት በቦታው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ህዝቡ ጨዋነት በተላበሰ ሁኔታ ሰልፉን ጠብቆ ምርጫውን እያከናወነ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱም ሰላማዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመካነ ኢየሱስ ቁጥር አንድ ምርጫ ጣቢያ ሲመርጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ ዮሴፍ ዮሃንስ በሰጡት አስተያየት፤ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ያለማንም ጣልቃ ገብነት እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

የምርጫ ሂደቱን ለመታዘብ የሲዳማ ህዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ወክለው የተገኙት አቶ ጴጥሮስ ቦልካ ከድምጽ አሰጣጡ አስቀድመው በምርጫ ጣቢያው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ምርጫው ከመጀመሩ በፊት ኮሮጆ ባዶ መሆኑን ተረጋግጦና ታዛቢዎች በተገኙበት የድምጽ አሰጣጡ መጀመሩን ጠቅሰው እስካሁን ያጋጠመ ችግር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በሌላኛው ምርጫ ጣቢያ የተገኙት አቶ ታከለ ዮሃንስ በበኩላቸው፤ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ማለዳ 11 ሰዓት ታዛቢዎችና የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በተገኙበት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ማስጀመራቸውን ገልጸው ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ድምጹን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም