በሮቤ፣ ጎባ፣ መቱና አዳማ ከተሞች መራጮች ድምጽ እየሰጡ ነው

78

ጎባ /አዳማ/መቱ ሰኔ 14/2013 በኦሮሚያ ክልል በሮቤ፣ ጎባ፣ መቱና አዳማ ከተሞች መራጮች ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እየተካሄደ ነው።

በባሌ ዞን ጎባና ሮቤ ከተሞች በሚገኙ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ተጀምሯል።

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የምርጫ ታዛቢዎች በተገኙበት ኮሮጆዎች ባዶ መሆናቸውን ተረጋግጦ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተጀምሯል።

በተለይም በሮቤ ከተማ ኦዳ የምርጫ ጣቢያ ላይ አቶ ካሳሁን ጎፌ ድምጽ ሰጥተዋል።

በባሌ ዞን በአምስት የምርጫ ክልሎች ስር በተቋቋሙ 552 የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍርዲሳ ጋሮምሳ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በአዳማ ከተማም ህዝቡ በሰላማዊ ሁኔታ ድምጹን እየሰጠ ይገኛል።

ብልፅግናን በመወከል በአዳማ ከተማ ገንደ ሃራ ምርጫ ጣቢያ አራት ድምፃቸውን የሰጡት ዶክተር ተሾመ አብዶ እንደገለፁት ህዝቡ ዝናብ ሳይበግረው ድምፅ እየሰጠ ይገኛል።

የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑንም ገልጸዋል።

በጠደቸ አራራ ቀበሌ በምርጫ ጣቢያ ሀ ድምፃቸውን የሰጡት የኢዜማ ተወካይ አቶ ሚሊዮን በጋሻው እንደተናገሩት የእስከ አሁኑ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ነው።

ሌላኛው ድምፅ ሰጪ ዶክተር አለማየሁ ግርማ ህዝቡ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ እየሰጠ ይገኛል።

ሂደቱም ሰላማዊ እንደነበር ብልፅግናን ወክለው ለጨፌ ኦሮሚያ የተወዳደሩት ዶክተር አለማየሁ ግርማ ተናግረዋል።

በዞኑ 1ሺህ 540 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ከዞኑ የምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በኢሉባቦር ዞን በሚገኙ ስድስት የምርጫ ክልሎች ሥር በተቋቋሙ 506 የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮች ዛሬ ከ12 ሰዓት ጀምሮ ድምፃቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።


የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቱ በሰላም በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ በዞኑ የተለያዩ ምርጫ ክልሎች ኃላፊዎች ገልጸዋል።

በኢሉባቦር ዞን መቱ ከተማም ኢዜአ ያነጋገራቸው መራጮች ለሀገር ዕድገት ይሠራል ብለን ላመንበት ፓርቲ ያለማንም ተፅዕኖ ድምጻቸውን እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ እጅጉ አጋ ከማለዳው 11 ሰዓት ጀምሮ በመቱ ከተማ ለጋ ሚሶማ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፃቸውን ለሀገር ይጠቅማል ብለው ላመኑበት ፓርቲ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

በከተማው አባ ሞሌ ምርጫ ጣቢያ ቁጥር ሁለት ድምጿን የሰጠችው ወጣት እታለም እድሪስ በበኩሏ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለፈለገችው ፓርቲ ድምጻን መስጠቷን ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም