በአማራ ክልል "እመርጣለሁ አረንጓዴ አሻራየን አኖራለሁ " የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ተጀመረ

70

ባህር ዳር ኢዜአ ሰኔ 14/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል'' እመርጣለሁ አረንጓዴ አሻራየን አኖራለሁ'' በሚል መርሃ ግብር ከ13 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመላለም ምህረት ለኢዜአ እንዳሉት፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር በማያያዝ የችግኝ ተከላ በተለያዩ አካባቢዎች ተጀምሯል።

የችግኝ ተከላው የተጀመረውም ዝናብ በጣለባቸው የከተማና ገጠር አካባቢዎች መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም  የሚሆን ችግኝና የመትከያ ጉድጓድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

''እመርጣለሁ አረንጓዴ አሻራዮን አኖራለሁ''  የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆንም በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች በየምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ሙያዊ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በክልሉ በክረምቱ በአረንጓዴ አሻራ ልማትና መደበኛ ፕሮግራም ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በክረምቱ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራምም 190 ሺህ ሄክታር መሬት ደን የማልበስ ስራ እንደሚከናወን አብራርተዋል።

በክልሉ የዘንደሮ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በተገኙበት በቅርቡ በደብረ ማርቆስ ከተማ ማስጀመራቸውን አዜአ በወቅቱ  ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም