የሲኖዶሶች የዕርቀ ሰላም የማብሰሪያ መርሃ ግብር በሚሊኒየም አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው

110
አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሶች የዕርቀ ሰላም ማብሰሪያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው። በኢትዮጵያና በአሜሪካ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ችግር ላለፉት 26 ዓመታት ሲኖዶሱ ለሁለት ተከፍሎ ቆይቷል። የእርቀ ሰላም ልዑካን ቡድን አስቀድሞ ሄዶ የሰራውን የማስታረቅ ስራ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአሜሪካ በመገኘት የረዥም ጊዜ ችግር ለመፍታት እርቅ እንዲወርድ አድርገዋል። በዚህም ሁለቱ ሲኖዶሶች ቃለ ውግዘታቸውን አንስተው ወደ ዕርቅ መምጣታቸው ይታወሳል። በፕሮግራሙም ስደተኛው ሲኖዶስ ተብሎ የሚጠራውና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ 4ተኛ ፓትሪያሪክ የሚመራው ሲኖዶስ ዛሬ በእናት አገሩ ከምዕመናን ጋር እግዚአብሔርን እያመሰገነ ይገኛል። በፕሮግራሙ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ቤተ እምነት አባቶች እንዲሁም  ከ25 ሺህ በላይ የእምነቱ ተከታዮችና ሌሎችም ተገኝተዋል። የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶሶች ለሁለት ሲከፈሉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ያመለክታል። አቡነ መርቆርዮስ ቡራኬ በመስጠት፣ አባ ማቲያስ ደግሞ አስተዳደራዊ ተግባራትን በመፈጸም ቤተክርስቲያኗን ያስተዳድራሉ። በሁለት ሲኖዶሶች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ በተካሄደው የሰላም ማብሰሪያ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቀጣይ የሁለቱ ሲኖዶሶች የሰላም ማብሰሪያ የማጠቃለያ ጉባኤ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ መጠቆማቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም