ይበጀናል ያሉትነ ወኪል ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የመተሃራ ከተማና ፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
ይበጀናል ያሉትነ ወኪል ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የመተሃራ ከተማና ፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ

አዳማና መቱ፤ ሰኔ 13/2013 (ኢዜአ) ነገ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በካርዳችን ይበጀናል የምንለውን ወኪል ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ የመተሃራ ከተማና ፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ።
በኢሉባቦር ዞን ለምርጫው የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተጓጓዙ መሆኑም ተገልጿል።
የመተሃራ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ ፈይሳ ባቲ ለኢዜአ እንደገለፁት "ህገ መንግሥቱ የሰጠንን ዴሞክራሲያዊ መብት ተጠቅመን የሚበጀንን እንመርጣለን" ብለዋል።
"አንድ ካርድ ለዴሞክራሲ ዋጋ አላት" ያሉት አቶ ፈይሳ አንድም ካርድ መባከን የለባትም" ሲሉም ተናግረዋል። ።
"ህዝቡ ለሀገር የሚበጀውን ያውቃል፤ ሀገራችንን ለሚያሻግርና ለሚጠቅመን ወኪላችን በካርዳችን ድምፃችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል" ብለዋል ።
"ሰላም ከሁሉም በላይ እኛን ነው የሚጠቅመው" ያሉት አቶ ፈይሳ መራጩ ህዝብ በሰላም ወጥቶ ድምፁን በመስጠት በሰላም ወደ ቤቱ እንዲመለስ ከፀጥታ ሃይል ጋር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመተሃራ ከተማ ነዋሪ ወጣት አልይ አብዶ በበኩሉ ዘንድሮ የሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወጣቶችን በተመራጭነትና በመራጭነት በስፋት ያሳተፈ መሆኑን ገልጿል።
"የከተማዋ ወጣቶች የሚጠቅመንን ለመምረጥ ከመዘጋጀታችን ባለፈ በቅድመ ምርጫ የነበረው ሰላማዊ ሂደት በድምፅ መስጫ ዕለትና ድህረ ምርጫ ላይም ሰላማዊ እንዲሆን ከፀጥታ አካላት ጎን ሆነን እየሰራን ነው" ብለዋል።
"በተለይም የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለወጣቶች ተስፋ የሰጡ እንቅስቃሴዎች የታዩበት በመሆኑ ድምፃችንን ለሚጠቅመን አካል ለመስጠት ካርዳችንን አዘጋጅተን ነገ ጠዋት ከንጋት 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ እንሰጣለን" ብለዋል ።
"ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው" ያሉት ደግሞ በፋንታሌ ወረዳ የመርቲ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፍቃደአብ ወልዴ ናቸው።
ህብረተሰቡ ተደራጅቶ አካባቢውን እየጠበቀ መሆኑን ጠቁመው "በተለይም የአካባቢውን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱን በማጋለጥና የፀረ ሰላም ሃይሎች እንቅስቃሴ እንዳይኖር ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር እየሰራን ነው" ብለዋል ።
"ነገ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ሀገርና ህዝብን ያሻግራል ብለው ላመኑት ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመጓጓዝ ላይ መሆናቸውን በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኢሉባቦር ዞን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኢሉባቦር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አንቢሳ እንዳሉት ሰኔ 14 ቀን 2013 ለሚካሔደው ምርጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሰሶች ወደ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች እየተጓጓዙ ነው፡፡
ጸጥታና ሰላምን በተመለከተ ችግር እንዳላጋጠመና የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡
በዞኑ በሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጠቢያዎች ለመምረጥ የተመዘገቡ 370 ሺህ 392 መራጮች ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሃላፊው አመላክተዋል።
በኢሉባቦር ዞን በስድስት ምርጫ ክልሎች ስር በተቋቋሙ በ506 ምርጫ ጣቢያዎች 2 ሺህ 530 የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመድበው ለምርጫው ዝግጅት መደረጉን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።