በቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች እንድትሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ ነው

83
አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚካፈሉ ተወዳዳሪዎች ስልጠና እንዲያገኙና በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የማጣሪያ ውድድሮች ለመሳተፍ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን የስፖርት ፌዴሬሽኖች ገለጹ። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2020 በሚካሄደው የጃፓን ቶኪዮ 32ኛው የኦሎምፒክ ውድድር በአትሌቲክስ፣ በቦክስ፣ በእግር ኳስ፣ በብስክሌት፣ በውሃ ዋና፣ በካራቴ፣ በወርልድ ቴኳንዶና ዒላማ ተኩስ ስፖርቶች ለመሳተፍ እቅድ ይዛላች። ኢዜአ የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች የስራ ሃላፊዎችን በዝግጅቱ ዙሪያ አነጋግሯል። የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው መኮንን በቶኪዮ ኦሎምፒክ በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ ተሳትፎ እንድታደርግ ተወዳዳሪዎች ዓለም አቀፍ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።  በቶኪዮ ኦሎምፒክ ውጤታማ ለመሆን በስዊዘርላንድ የኢንተርናሽናል ብስክሌት ማህበር ማዕከል እየሩ ተስፎምና ሚሊዮን ቤዛ ስልጠና እየተከታተሉ መሆናቸውንና በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም ስልጠናቸውን እንደሚያጠናቅቁ ገልጸዋል። ሬድዋን ሳሊህ፣ክፍሎም ገብረመድህንና ተመስገን መብራህቱ በደቡብ አፍሪካ የ 3 ወር ስልጠና ወስደው መምጣታቸውን አስታውሰዋል። በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በትግራይ መቀሌ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ብዙ ልምድ ያካበቱትን ተወዳዳሪዎች ያሸነፉ ብስክሌተኞች በአህጉራዊ ማጣሪያዎች የመሳተፍ እድል እንደሚያገኙ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት በቶኪዮ አሎምፒክ የመሳተፍ እድሉን እንድታገኝ በ2011 ዓ.ም 17ኛውን የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርባ ከአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌዴሬሽን ምላሽ እየተጠባበቀች መሆኑን ጠቁመዋል። አገሪቷ ውድድሩን ብታዘጋጅ ብዛት ያላቸውን ብስክሌተኞች በሻምፒዮናው በማሳተፍ ውጤታማ በመሆን በቶኪዮ ኦሎምፒክ በሁለቱም ጾታዎች የመሳተፍ እድሏን ማስፋት እንደምትችል ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ በበኩላቸው በቶኪዮ ኦሎምፒክ በቦክስ ስፖርት ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ኢትዮጵያ በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም በሞሮኮ ካዛብላንካ በተካሄደው የአፍሪካ የወጣቶች የቦክስ ሻምፒዮና ሁለት ወርቅና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቷ በቶኪዮው ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ለሚደረገው ጥረት የሞራል ስንቅ ይሆናልም ብለዋል። የሞሮኮው ውድድር ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ያለባቸውን ክፍተት በማየት ብቃታቸውን እንዲያሻሽሉ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ እንደነበርም አውስተዋል። በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በሚካሄድው የዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ ሀና ደረጀና እንዳሻው አላዩ በውድድሩ የሚሳተፉ ሲሆን ለውድድሩ ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል። የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከሁለት ዓመት በፊት በብራዚል ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የካራቴ ስፖርት በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ እንዲካተት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የሰጠውን እድል በመጠቀም በመጀመሪያው ውድድር ተሳታፊ ለመሆን በአህጉር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ለመሳተፍ የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀቱንም የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ አንጀሎ ገልጸዋል። በኦሎምፒክ ውድድር ለመሳተፍ በተዘጋጀውና በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ከነሐሴ 25 እስከ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው የአፍሪካ ካራቴ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለኪጋሊው ውድድር በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተወዳዳሪዎችን የመመልመል ስራ መጀመሩንም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ለቶኪዮው ኦሎምፒክ ቅድመ ዝግጅት ይረዳ ዘንድ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቋሞ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል። ከሌላው ጊዜ በተጠናከረ መልኩ በመደጋገፍና በመመካከር እንዲሁም በህብረት በመስራት አገሪቷ በኦሎምፒክ የምትሳተፍባቸው ስፖርቶች ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። በዚህም ረገድ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ስፖርተኞች በአካዳሚው ስልጠና እንዲያገኙና ልምምድ እንዲያደርጉ ትብብር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች የሚገኙ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ብቁ ናቸው የሚባሉ ተወዳዳሪዎችን የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ዶክተር አሸብር ያስረዱት። ኦሎምፒክ ኮሚቴው ለውድድሩ ይረዳ ዘንድ በተለያዩ ስፖርቶች በሚካሄዱ ማጣሪያዎች ስፖርተኞች እንዲሳተፉ የውድድር አማራጭ እየፈጠረ እንደሆነም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ እቅድ የያዘችባቸው ስፖርቶች በጥናት የተመረጡና በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አበረታች ውጤቶች የመጣባቸው መሆኑን አመልክተዋል። በቶኪዮ ኦሎምፒክ አንጋፋ ስፖርተኞችና ተስፋ ሰጪ የሆነ ብቃት እያሳዩ ያሉ ተወዳዳሪዎችን ቀላቅሎ በማሳተፍ ጥሩ ውጤት ለማስመዘገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። በአልጄሪያ በተካሄደው 3ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ እንዲሁም በቀጣይ ዓመት በአርጀንቲና በሚካሄደው የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ፣የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታና የመላው አፍሪካ ጨዋታ የሚገኙ ተወዳዳሪዎች ለቶኪዮው ውድድር ግብአት ይሆናሉ ብለዋል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተለያዩ ስፖርቶች እያስመዘገበችው ያለችው ውጤት በቶኪዮ ኦሎምፒክ በተሻለ የስፖርት ቁጥር ለመሳተፍ ያላትን እድል የሚያሰፋ ነው ብለዋል። በተደረጉ ግምገማዎች ቅርጫት ኳስና እጅ ኳስ ውድድሮች ከሌሎቹ ከታቀዱት 8 ስፖርቶች በተጨማሪ በእቅድ ውስጥ ለማካተት ሀሳብ እንዳለ ጠቁመዋል። የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሩቅ ነው ወይም ቅርብ ነው ማለት እንደማይቻልና ከወዲሁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅትና ርብርብ ተደርጎ ኢትዮጵያ ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም