መንግስት የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን ፈጥኖ በመለየት መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል… የሸካ ዞን ነዋሪዎች

1458

ሚዛን ሀምሌ 28/2010 መንግስት የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን ፈጥኖ በመለየት መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ የሸካ ዞን ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

የደኢህኤን ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በደቡብ ምዕራብ በሚገኙ ካፋ፣ ሸካና ቤንቺ ማጂ ዞኖች ያደረጉት የሦስት ቀናት የህዝብ ውይይት ትናንት በቴፒ ከተማ ተጠናቋል፡፡

ሊቀመንበሯ በፔቲ ከተማ ከሸካ ዞን ነዋሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይትም ነዋሪዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን መንግስት ለጥያቄቸው ትኩረት ሰጥቶ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል ከየኪ ወረዳ የመጡት አቶ በዛብህ በየነ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚና ተሳታፊ የሚሆኑበት ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

“ነባር ብሄር በሚል አስተሳሰብ የዞኑ ተወላጅ ላልሆኑ ዜጎች የሚሰጠው ቦታና ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው ይህም በዜጎች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር፣ መጠራጠር እንዲኖርና እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓል ብሏል፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ዕድል እንዲኖረውና ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ጠይቀዋል፡፡

ሌላኛው የቴፒ ከተማ ነዋሪ መምህር ኢዮብ አስራት በበኩላቸው በሸካ ዞን ባለፉት ዓመታት ግጭቶችና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

የተፈጠሩት ግጭቶች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ውድመት ቢያደርሱም ለግጭቶቹ ምክንያት የነበሩ አመራሮች ተጠያቂ ሳይሆኑ ወደተሻለ የአመራርነት ደረጃ እንዲዛወሩ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ችግሩ አሁንም እንዳልተፈታና በማህበረሰቡና በብሔሮች መካከል መቃቃርና መጠራጠር በመፈጠሩ ዞኑም ሆነ የቴፒ ከተማ በተፈለገው ሁኔታ መልማት እንዳይችሉ አድርጎ መቆየቱን ገልጽዋል፡፡

መንግስት የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ መፍትሔ እንዲሰጥና ጥፋተኞችን ተጠያቂ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በአካባቢያቸው ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት ችግር እንዳለ የገለጹት ደግሞ የማሻ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ሶፊያ ሃቢብ ናቸው፡፡

በአብነትም ከቴፒ ማሻ ያለው መንገድ የተጎዳና አስቸጋሪ መሆኑና የማሻ ሆስፒታል ተጀምሮ ለበርካታ አመታት አለመጠናቀቁን  ጠቅሰዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይልና የመሰረት ልማት ተጠቃሚ አለመሆን፣ የዞኑ የደን ሃብት አላአግባብ በባለሃብቶች መጨፍጨፍና የወጣት ሥራ አጥነት መበራከት ነዋሪዎቹ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ይገኙበታል።

ተገቢ ያልሆነ የግብር ትመና፣ የፍትህ መጓደልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችም እንዲሁ የተነሱ ቅሬታዎች ናቸው ፡፡

የደኢህዴን ሊቀ መንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው መንግስት ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ አለመስራቱ ህዝባዊ ቅሬታዎቹ በዚህ ደረጃ የሰፉና የገዘፉ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ቀጣይነት ያለው ውይይት እንደሚደረግና ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ስለመመለሳቸው የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሰራ  ተናግረዋል፡፡

“ህብረተሰቡ ያነሳቸው የሰላም ጥያቄዎች ቅድመ ሁኔታ የሚሰጣቸው ባለመሆኑ መንግስት ፈጥኖ ሰላሙን የማረጋገጡን ተግባር ያከናውናል” ብለዋል፡፡

ህዝቡ ጥፋተኛ የተባሉ አመራሮችን በተመለከተ ላነሳው ጥያቄም ጉዳዩን በማረጋገጥ ተጠያቂ እንደያሚደርግ ገልጸዋል፡፡

“በአመራሩና በወጣቱ መካከል ያለው ግንኙነት የተዛባ በመሆኑ ጤናማ ግንኙነት እንዳይፈጠር አድርጓል” ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት ሰፊ ቁጥር ያለውን ወጣት በሥራ ዕድል ፈጠራ በማሰመራትና ፍላጎቱን በማድመጥ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የማሻ ሆስፒታል ጥያቄ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ፈጥኖ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፣ ግብርን በተመለከተ ክልላዊ ችግር ቢኖርም ያለንግዱ ማህበረሰብ አገር መገንባት ስለማይቻል ችግሩ በቅርበት እንደሚፈታ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በሦስቱ ዞኖች በነበራቸው ቆይታ በዋናነት የአመራር ድክመት፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና የቆዩ ግጭቶች በመኖራቸው እልባት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

በሦስቱም ዞኖች ያለውን የመልማት አቅም በተፈለገው ሁኔታ መጠቀም አልተቻለም ያሉት ሊቀመንበሯ፣ ደኢህዴንም በአካባቢው ያሉ የሕዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከዚህ በፊት ይከተለው ከነበረው የድጋፍና ክትትል ስልት በተለየ ሁኔታ እንደሚሰራ አስረድተዋል።