በኢሉአባቦር ዞን ከ90 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው

71
መቱ ሀምሌ 28/2010 ህብረተሰቡ  ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለእንክብካቤ ትኩረት ስጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የሰግለን ኢሉ አባገዳ ከሊፋ ጫሊ አሳሰቡ፡፡ በኢሉአባቦር ዞን በክረምት ወቅቱ ከ90 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ  የችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው፡፡ በዞኑ ያዮ ወረዳ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የሰግለን ኢሉ አባገዳ ከሊፋ ጫሊ እንዳስገነዘቡት የሚተከለው ችግኝ ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ ካልተደረገለት የጽድቀት መጠኑ አነስተኛ ነው፡፡ ህብረተሰቡም ይሄንን በመገንዘብ በግልና በጋራ በመሆን ለተከለው ችግኝ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ “ከገዳ ስርአት አስተምህሮቶች ውስጥ አንዱ ለደኖችና በውስጡ ለሚኖሩት የዱር እንስሳት ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ ነው” ያሉት አባገዳው ህብረተሰቡ ይህንኑ አስተምህሮት ለትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ህብረተሰቡ በየአመቱ ከሚተክለው የዛፍ ችግኝ በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኘውና በተባበሩት መንግታት ድርጅት የትምህርት ባህልና የሳይንስ ማዕከል(ዩኒስኮ) የተመዘገበውን የያዩ ተፈጥሮ ደንን በአግባቡ በመንከባከብ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የያዮ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱ መሀመድ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው በየአመቱ እየተተከሉ ያሉት የዛፍ ችግኝ የአካባቢ መራቆትን በመቀነስ ለደን ሽፋኑ መጨመር አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ችግኙ እንዲፀድቅም በግልና በጋራ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ የኢሉአባቦር ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታሁን ለገሰ በበኩላቸው ህብረተሰቡ የዛፍ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ  ማድረግ እንዳለበት ተከታታይ ትምህርት እየተሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው አመት ከተተከለው ከ130 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የዛፍ ችግኝ ውስጥ ከ88 ከመቶ በላይ የሚሆነው በተደረገው ጥበቃና እንክብካቤ መጽደቁን ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮው ክረምት በ23 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ከታቀደው ከ90 ሚሊዮን በላይ የዛፍ ችግኝ ውስጥ እስካሁን ከ80 ሚሊዮን በላይዩ ተተክሏል፡፡ በችግኝ ተከላውም ከ200ሺ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ የኢሉአባቦር ዞን  ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ ከሚሆነው ስፋቱ ግማሽ ያህሉ በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ከዞኑ የደን ሽፋን ውስጥም ከ167ሺ ሄክታር በላይ የሚሆነው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ባህልና ሳይንስ ማዕከል (ዩኒስኮ) በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የያዮ ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም