ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በመሳተፍ ኢትዮጵያን አረንጓዴ እንዲያለብሱ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2013 /ኢዜአ/ ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በመሳተፍና ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ለመጪው ትውልድ የበለፀገች አገር እንዲያስረክቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ረፋድ ላይ ቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

"የተፈጥሮ ሐብታችንና ነፃነታችንን በመጠበቅ ለሁሉም የምትመች አገር እንገነባለን" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተሳትፎ በማድረግና ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ለመጪው ትውልድ የበለፀገች አገር እንዲያስረክቡም አሳስበዋል፡፡

ለዚህ ይረዳ ዘንድ ወጣቶች በነቂስ ወጥተው ችግኝ እንዲተክሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግስት ለአገር ሠላም፣ አንድነትና ልማት ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመር ልማት በሁሉም ቦታ ለማድረስ የያዝነውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በመንገድ፣ በጤናና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም