ኮርፖሬሽኑ ከ14ሺህ ሄክተር በላይ መሬት ላይ ምርጥ ዘር ለማባዛት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

96

አዳማ፤ ሰኔ 10/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በተያዘው የመኸር ወቅት ከ14ሺህ ሄክተር በላይ መሬት ላይ የተለያየ የሰብል ምርጥ ዘር ለማባዛት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ከ3ሺህ በላይ ሄክተር በተለያየ የምርጥ ዘር ማባዛት ጀምሯል።

በዚህ ወቅት በኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘርና የደን ውጤቶች ዘርፍ ምክትል ስራአስፈፃሚ አቶ ዘነበ ወልደስላሴ እንደተናገሩት፤ በመኸሩ ወቅት 19 ዓይነት ምርጥ ዘር ለማባዛት እየተሰራ ነው።

ከሚባዘው የሰብል ዓይነት ውስጥ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ አተር፣ ባቄላና ሰሊጥ ይገኙበታል።

ኮርፖሬሽኑ በ2012/2013 የምርት ዘመን 284 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ማዘጋጀቱን የገለጹት፤ አቶ ዘነበ በተያዘው የምርት ዘመን ደግሞ ከ330ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማባዛት ርብርብ እያደረግን ነው ብለዋል።

በዘር ብዜቱ አርሶ አደሩ፣ ባለሃብቶችና ኮርፖሬሽኑ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑ አስረድተዋል።

ለስራው  ውጤታማነት በቂ የምርት ማሳደግያ ግብዓት መቅረቡን ገልጸው፤ በተለይ በሜካናይዜሽን የእርሻ መሳሪያዎች እየታገዝን መሬቱን በዘር እየሸፈንን ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩም ጭምር የሜካናይዜሽን አገልግሎት ከማመቻቸት ባለፈ ከእርሻ ማዕከላት ጋር በትብብር በመስራት ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሁለገብ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮርፖሬሽኑ የአርዳይታ እርሻ ማዕከል ሃላፊ አቶ መሃዲ አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ባለፈው የምርት ዘመን 87 ሺህ ኩንታል ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ አተርና ጎመን ምርጥ ዘር ማምረቱን ገልጸዋል።

ማዕከሉ አምና የዕቅዱን 89 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቅሰው የተመረተው ሰብል በዶዶላ፣ ኮፈሌና አሰላ ተዘጋጅቶ በኮርፖሬሽኑ በኩል ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ተደርጓል ብለዋል።

በተያዘው የመኽር ወቅት በማዕከሉ 3ሺህ 100 ሄክታር እስከ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ዘር ለመሸፈን ርብርብ እያደረግን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም