የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወር ተግባር የሚመራው አማካሪ ምክር ቤት ስራውን ጀመረ

1946

አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወሩን ተግባር የሚከታተል የአማካሪ ቡድን በይፋ ስራ መጀመሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ አስታወቁ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ባሳለፍነው ግንቦት ላይ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ሙሉ ለሙሉና በከፊል ወደ ግል ይዞታነት እንዲዛወሩ መወሰኑ ይታወሳል።

በዚህ ውሳኔ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወሩን ሂደት የሚከታተል 21 አባላት ያለው የአማካሪ ቡድን ማቋቋማቸውን አቶ ፍጹም ለኢዜአ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ፍጹም ገለጻ፤ የአማካሪ ቡድን አባላቱ የተመረጡት ያላቸውን የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ልምድን መሰረት በማድረግ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በሚወክል መንገድ ተመርጠዋል።

በዚህም አማካሪ ምክር ቤቱ ትናንት በይፋ ስራ እንደጀመረ የገለጹት አቶ ፍጹም፤ ስራው ኢትዮጵያ የገጠማትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚፈታ፣ ግልጽና ተጠያቂነትን ባሰፈነ መንገድ እንደሚያከናውኑም ተገልጿል።

የአማካሪ ምክር ቤቱ አባላትም አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ፣ አቶ ዘላለም መለሰ፣ ዶክተር አለማየሁ ስዩም፣ ወይዘሮ መአዛ ብሩ፣ አቶ በቀለ ገለታ፣ አቶ አበበ አእምሮሥላሴ፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ ወይዘሮ ሳራ አበራ፣ ዶክተር አይናለም መገርሳ፣ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና፣ ዶክተር ጸጋይ በርሄ፣ ዶክተር ተገኝወርቅ ጌቱ፣ አቶ ካሳ ከበደ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አቶ ሌንጮ ባቲ፣ ዶክተር አብራሃም ተከስተ፣ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እና አምባሳደር ግርማ ብሩ ናቸው።