የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች በከተሞቹ ባለመኖራቸው ለችግር ታጋልጠናል— የሆሳዕና እና ጭሮ ነዋሪዎች

980

ሆሳእና/ጭሮ ሀምሌ 27/2010 ጎርፍን ጨምሮ የፍሳሽ  ማስወገጃ  ቦዮች በመደፈናቸውና ባለመሰራታቸው ለችግር መጋለጣቸውን በሆሳዕና እና ጭሮ ከተሞች ነዋሪዎች  ገለጹ፡፡

በሆስዕና ከተማ የሜላምባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብድልፈታ ጀማል ለኢዜአ እንዳሉት በአካባቢያቸው ያለው የፍሳሽ ማስወገጃ በቆሻሻ ተደፍኗል፡፡

በዚህም ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጣው ፍሳሽ በመታቆሩ ምክኒያት በሚፈጠረው ሽታ  ለጉንፋንና መሰል ችግሮች መጋለጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቦዮቹ መደፈን አካባቢውን ለጎርፍ ተጠቂ እንደሚያደርጋቸውና በተሰማሩበት የንግድ ስራ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩንም ጠቁመዋል፡፡

“ፍሳሹ የትም መንቀሳቀሻ ስለሌለው ማንኛውም ውሃ በመከማቸቱ ከፍተኛ የሆነ ሽታ አምጥቷል፤ለበሽታም እየዳረገን ተቸግረናል” ያሉት ደግሞ በከተማው የንግድ ባንክ ሰራተኛ የሆኑት አቶ ዮናስ ዮሐንስ ናቸው፡፡

አቶ ስዩም ሸርጦሬ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በከተማው ውስጥ  በተለይም ከመናኸሪያ እስከ አደባባይ ድረስ ባለው አካባቢ ዝናብ በሚሆንበት ወቅት ፍሳሹ ወደ ማስወገጃው ስለማይገባ ጎርፍ መሃል አስፓልት ላይ እንደሚተኛ አመልክተዋል፡፡

በሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤት የከተሞች ማስፈጸም አቅም ግንባታ ህብረተሰብ ተሳትፎ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ በቀለ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ክፍት በመሆኑ ሕብረተሰቡ በሚጥለው  ቆሻሻ ምክንያት ቀዳዳዎቹ መደፈናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ፍሳሹ ወደ አስፓልትና አንዳንዴም ባለበት ታቁሮ በመቀመጡ ለህብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአስፓልት መንገዱ ከአዲስ አበባ ሃዋሳ አርባምንጭ የሚዘልቅ  ዋናው አውራ ጎዳና  በመሆኑ የመንገድ ዳር ቦዮች ዲዛይን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጠንቶ ወደ ትግበራ እየተገባ በመሆኑ  ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል፡፡

“ህብረተሰቡን በማስተበባበር የሚከናወን የከተማ ጽዳት ስራ ተፈጻሚነት በመዳከሙ የተፈጠረ ችግር ነው ” ስራ አስኪያጁ “በቀጣይ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ክትትል የማድረግ ስራ ይከናወናል” ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ በቂ የጎርፍ ማስወገጃ ቦይ ባለመሰራቱ ክረምት በገባ ቁጥር ለችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በጭሮ  የቀበሌ አንድ  ነዋሪ አቶ ተፈሪ በሻ እንዳመለከቱት እሳቸውን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪ ክረምት በገባ ቁጥር በስጋት ነው የሚያሳልፉት፡፡

በከተማዋ በየጊዜው የሚሰሩ ቤቶች በጥናት ላይ የተመሰረቱ ባለመሆናቸውና በቂም የጎርፍ መከላከያ ባለመሰራቱ ጎርፉ መሄጃ በማጣት ወደ መኖሪያ ግቢያቸው እየገባ ጉዳት እያደረሰባቸው ይገኛል።

ዝናብ በጣለ ቁጥር የሚፈጠረው ጎርፍ መሄጃ በማጣት መንገዱን ስለሚያጥለቀለቅ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እያስተጓጎለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባለ ሶስት እግር ታክሲ አሽከርካሪ የሆኑት አቶ አስቻለው ኪዳነማርያም ናቸው።

ይህ በተሽከርካሪያቸውና  በቀን ገቢያቸው ላይ ተጽዕኖ በማስከት ለችግር እንዳጋለጣቸው ተናግረዋል።

ወይዘሮ አሰገደች በለጠ የተባሉት ነዋሪ እንዳሉትም እየጣለ ያለው ዝናብ በዚሁ ከቀጠለ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል የጎርፍ መከላኪያ በፍጥነት ሊሰራ ይገባል።

ጎርፍ መሄጃ በማጣት ወደ ቤታቸው እየገባ ስጋት እንደሆነባቸውም ጠቁመዋል።

በጭሮ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የመሰረተ ልማት የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አስራት መስፍን የነዋሪዎቹ ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አምነው ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተዳደር በመደበው 4 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የጎርፍ ማስወገጃ ቦይ ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡

ከተማዋን ከጎርፍ ለመታደግ የሚከናወነው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት የስራ ሂደቱ ባለቤት  ስራው ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ  አቅም በፈቀደ ስራውን በማፋጠን ነዋሪውን ከስጋት  ለመታደግ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።