ምርጫውን ተከትሎ የሚመጡ ክርክሮችን የሚመለከቱ ችሎቶች ተቋቁመዋል- የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች

65

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 09/2013 (ኢዜአ) ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ የሚመጡ ክርክሮችን የሚመለከቱ ችሎቶች መቋቋማቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች አስታወቁ።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ገዛሊ አባ ሲመል እንደገለጹት በክልሉ የሚመጡ ምርጫ ነክ ክርክሮችን የሚመለከቱ ችሎቶች ተቋቁመዋል፤ ዳኞችም ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

በዚህም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና  በ22 ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የምርጫ ነክ ችሎቶች መዋቀራቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም ለ304 የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች ስልጠና መሰጠቱን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዕቅድና በጀት ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ ዓለሙም በበኩላቸው ከምርጫ በፊትም ሆነ ከምርጫ በኋላ ለሚከሰቱ ክስተቶች ዳኞች ከሌላው በተለዬ ቅድሚያ ሰጥተው  የራሳቸውን ችሎት አዘጋጅተው እንዲሰሩ መመሪያ መሰጠቱ አንስተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዲሲፕሊን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሙሐሙድ የክልሉ ዳኞች ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ በምርጫና ድህረ ምርጫ የሚነሱ ክርክሮች ካሉ ለመዳኘት ችሎቶች  መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም