የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ በከተማው የተፈጠረውን የስንዴ እጥረት ለማቃለል የሚያስችል ስርጭት ማካሄዱን አስታወቀ

54
አዲስ አበባ ሐምሌ 27/2010 በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጠረውን የስንዴ እጥረት ለመፍታት በተያዘው ወር በቂ ምርት መሰራጨቱን የአስተዳደሩ ንግድ ቢሮ አስታወቀ። መንግስት በድጎማ የሚያቀርበው ስንዴ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በከተማዋ ሳይሰራጭ በመቅረቱ በዳቦ ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱን ገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ዛሬ በሰጠው መግለጫ መንግስት በድጎማ የሚያቀርበው ስንዴ በሰኔ ወር ሳይሰራጭ በመቅረቱ የተፈጠረውን እጥረት ለመፍታት በተያዘው ወር እጥረቱን ለማቃለል የሚያስችል ስርጭት ማካሄዱን አስታውቋል። በቢሮው የኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን በየነ እንዳሉት፤ በሐምሌ ወር 165 ሺህ 657 ኩንታል ጥሬ ስንዴ በከተማዋ ተሰራጭቷል። በተጨማሪም 120 ሺህ ኩንታል ስኳር እና 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የፓልም ዘይት ለነዋሪዎች መሰራጨቱን ተናግረዋል። እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፤ ቢሮው ለሸዋ ዳቦ፣ ለአፍሪካ ዳቦና ለምሥራቅ ዳቦ ቤቶች በቀጥታ የጥሬ ስንዴ አቅርቦት ያደረገ ሲሆን የገበያ ትስስር ለፈጠሩ 1 ሺህ 600 ዳቦ ቤቶች ከስንዴ ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች ዱቄት እየቀረበላቸው ነው። መንግስት በቀጥታ ጥሬ ስንዴ ለሚያቀርብላቸው ሦስት ዳቦ ቤቶች እና ለ37 የዱቄት ፋብሪካዎች በቂ የስንዴ አቅርቦት የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ለከተማዋ ነዋሪዎች በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት በኩል የስንዴ ዱቄት፣ የስኳርና የፓልም ዘይት በበቂ መጠን እንዲቀርብ መደረጉን አስረድተዋል። የዱቄት ፋብሪካዎቹ ከመንግስት የተፈቀደላቸውን የስንዴ መጠን ከአዳማ፣ ከኮምቦልቻ እና ከሁሩታ መጋዘኖች እንዲወስዱ መደረጉን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ዳቦ ላይ ታይቶ የነበረው የዋጋ ጭማሪ ቅናሽ እንደታየበት አቶ ካሳሁን ጠቁመው በአንዳንድ ቦታዎች የምርት መደበቅ፣ የዋጋ መጨመርና ሚዛን ማጉደል ችግር መኖሩን ተናግረዋል። በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚታዩ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠር የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ቁጥጥር የሚያደርጉ አምስት ቡድኖች መዋቀራቸውን ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ባሉ ዳቦ ቤቶች የዋጋ ዝርዝር የግራም መጠን የሚለጠፍ መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን ከዚህ ውጪ በሚንቀሳቀሱ ዳቦ  ቤቶች ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ቢሮው ባካሄደው ቁጥጥር በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 74 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰዋል። በተጨማሪም ለ122 የንግድ ድርጅቶች የቃል ማስጠንቀቂያ እና ለ148 የንግድ ድርጅቶች ደግሞ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በዳቦ ቤቶች፣ በአትክልትና ፍራፍሬና በስጋ ቤቶች እንዲሁም በተመረጡ የንግድ ድርጅቶች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። ከሚዛን ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የንግድ ድርጅቶች የዲጂታል ሚዛን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም