"የኢትዮጵያን አንድነት ከማስጠበቅ አልፈን የአፍሪካ ቀንድን የአፍሪካ ክንድ እናደርጋለን "... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

63

ሰኔ 9/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያን አንድነት ከማስጠበቅ አልፈን " የአፍሪካ ቀንድን የአፍሪካ ክንድ እናደርጋለን " ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

የጅማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ብልጽግና ፓርቲን በመደገፍ ዛሬ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

በድጋፉ ሰልፍ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዳሉት የለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመርነውን ስራ ለማሳካት የሚያቆም ኃይል የለም፡፡

የኢትዮጵያን ህዝብ ይዘን ከኢትዮጵያ አልፍን ለአፍሪካ ብርሃን እናመጣለንም ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ከመፍረስ እንድትድን ያደረግናት በአንድነት፣ በህብረትና በመደማመጣችን ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "የአፍሪካ ቀንድን የአፍሪካ ክንድ" ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

"በምርጫው ዴሞክራሲን እንተክላለን፣ ዛፍም እንተክላለን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ " መላው ዓለም በምርጫ ቀን ይጋጫሉ ብሎ ሲጠብቅ፤ እኛ ደግሞ ችግኝ ተክለን ፍቅርን እናስተምራለን " ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ብልጽግና፣ ልማት፣ አንድነትና ህብረት ለሚሹ ፖለቲካ ፓርቲዎችም መልካም ዕድል ተመኝተዋል፡፡

የጅማ መገለጫ የሆነችው ባለ ሶስት እግር መቀመጫም ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ትርጓሜ እንዳላትም በዚሁ መድረክ ላይ   የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፤ ለኢትዮጵያ ብሎም ለመላው አፍሪካዊያን ሰላምና ብልፅግና ተመኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመለስ አብዲሣ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአመራርነታቸው ኢትዮጵያ የተከበረች፣ የአንድነትና የእኩልነት አገር እንድትሆን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስና በብዙ መሰናክሎች ውስጥ በማለፍም ''ድንቅ'' ብቃታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም