በጉጂ ዞን በሁለተኛው ዙር በመስኖ ከለማው ከ876 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል

94
ነገሌ ኀምሌ 27/2010 በጉጂ ዞን በሁለተኛው ዙር በመስኖ ከለማው አስካሁን ድረስ ከ876 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ቦሩ ገልገሎ እንዳስታወቁት በዞኑ ካለፈው የካቲት አጋማሽ ጀምሮ በተካሄደው ሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት ሥራ 8 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያየ ሰብል ለምቷል። በባህላዊ መንገድ ከለማው ከዚህ መሬት ውስጥ ከ1 ሚሊዮን 65 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያየ ምርት እንደሚጠበቅና እስካሁንም 876 ሺህ 910 ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል። ''በልማቱ እየተሳተፉ የሚገኙ 27 ሺህ 240 አርሶ አደሮች ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል''ብለዋል። ዘንድሮ በመስኖ የለማው መሬት ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር በ1 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ ሲሆን በምርትም በ142 ሺህ ኩንታል ብልጫ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። አቶ ቦሩ እንዳሉት በዞኑ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት 32 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል። በሊበን ወረዳ የኮባዲ ቀበሌ ከፊል አርሶ አደር አብዱል ቃድር አብዱላሂ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ከመጀመሪያው ዙር መስኖ ልማት 150 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግም በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት በባህላዊ መስኖ ያለሙትን የቃሪያ ፣ የቲማቲምና የቀይ ሽንኩርት ምርት በመሰብሰብ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። አጠቃላይ ምርቱን እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ ሙሉ በሙሉ ሰብስበው እንደሚያጠናቅቁ የጠቆሙት አርሶ አደር አብደላ ማሳቸውን ለቀጣዩ እርሻ ሥራ ዝግጁ ለማድረግ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል። "ከሁለተኛው ዙር መስኖ ልማት 120 ኩንታል የቲማቲምና የቀይ ሽንኩርት ምርት እጠብቃለሁ" ያሉት ደግሞ ሌላው የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ አልይ ሉሆ ናቸው። አቶ አልይ እንደሚሉት አሁን ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ዋጋ ጥሩ በመሆኑ በቀጣይ ልማቱን አስፋፍተው ለመስራት አቅደዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም