በድርቅ ምክንያት ያጣነውን ሰበል በበልግ አዝመራ ለማካካስ እየሰራን ነው...የሊበን ወረዳ ከፊል አርሶ አደሮች

154
ነገሌ ግንቦት 7/2010 ባለፉት ሁለት ዓመታት በድርቅ ምክንያት ያጡትን ሰበል በበልግ አዝመራ ለማካካስ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን በኦሮሚያ ከልል ጉጂ ዞን የሊበን ወረዳ ከፊል አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡ በከፊል አርብቶ አደሩ በዘር ከተሸፈነ መሬት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ አርብቶ አደር ልማት ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡ በዞኑ ሊበን ወረዳ የድቤ ጉቼ ቀበሌ አርሶአደር ተስፋዬ ቦነያ ባለፈው ዓመት በአካባቢያቸው በነበረው ድርቅ በ3 ሄክታር ማሳ ላይ የዘሩት የስንዴ ሰብል ሙሉ በሙሉ ደርቆ መቅረቱን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም የደረሰባቸውን ጉዳት ለማካካስ እያከናወኑት ባለው የበልግ አዝመራ 4 ሄክታር ማሳቸውን በስንዴ ዘር ሸፍነው ተገቢ እንክብካቤ በማድረጋቸው በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። "ምርቱን ለማሳደግ ከዘር ወቅት ጀምሮ እስካሁን ማሳዬን በማረምና በመንከባከብ ላይ እገኛለሁ" ብለዋል፡፡ በዞኑ አሁን ያለውን የተስተካከለና ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ በመጠቀም ከ4ቱ ሄክታር የስንዴ ማሳቸው ከ100 ኩንታል የሚበልጥ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ አቶ ጊሮ ጂሎ የተባሉት አርሶ አደር በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በተባይና በድርቅ ምክንያት ያጡትን ሰብል በበልጉ አዝመራ ለማካካስ እየሰሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በሰብላቸው አረምን ለመከላከል ከሚያከናውኑት ሥራ በተጨማሪ የበልጉ ዝናብ መጠንም ሆነ ስርጭት መጨመሩ የተሻለ ምርት ለማግኘት ተስፋ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ ለበልግ አዝመራ ካዘጋጁት ሦስት ሄክታር ማሳ ግማሹን በጤፍ፣ ቦለቄ፣ በቆሎና ስንዴ ሰብል ሸፍነው የተሻለ ምርት ለማግኘት ተገቢ እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን ሁለት ሄክታር በቆሎና ስንዴ እያለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ሁሴን ጫማ የተባሉ ነዋሪ ናቸው። ባለፉት ዓመታት በአካባቢው በነበረው ድርቅ በሰብልና በቤት እንስሳት ላይ ጉዳት ቢያደርስም በአሁኑ ወቅት ያንን ሊያካክስ የሚችል ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የዞኑ አርብቶ አደር ልማት ጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኢያሱ አሰፋ በበኩላቸው እንዳሉት በተያዘው የበልግ አዝመራ 96 ሺህ 486 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡ ስንዴ፤ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ቦለቄን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች በዘር ከተሸፈነው ከዚሁ መሬት 1ፈሚሊዮን 901 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡ ከፊል አርሶ አደሩ ምርታማነቱን ለማሳደግ የቀረበለትን ከ14 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ የፋብሪካ ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ አውሏል፡፡ በአርሶአደሩ እየለማ ያለው መሬት ባለፈው ዓመት ከለማው በ20 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሆኑ ምርቱም በ540 ሺህ ኩንታል ይበልጣል ተብሎ እንዲጠበቅ ያደረገው መሆኑን አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም