ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የነጆ ባለ 132/33 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ተመረቀ

119

ሰኔ 6/2013(ኢዜአ) ከአዲስ አበባ በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ከተማ የተገነባው ባለ 132/33 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ዛሬ በይፋ ተመርቋል።

በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያው መገንባት ባለሃብቶች እና ኢንቨስተሮች በአካባቢው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ እድል ይፈጥራል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ተመርቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ በኤሌክትሪክ ኃይል አና በሌሎች ዘርፎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሠረት ለማጠናቀቅ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ለአንድ ሀገር ሁሉ ነገር በመሆኑ በቀጣይ በክልሉ የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።

ባለሀብቶች የተፈጠረላቸውን ዕድል በመጠቀም በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሳተፍ አካባቢያቸውን ለመቀየር ጠንክረው እንዲሰሩም አሳስበዋል።የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ ትኩረት በማድረግ ለሀገር እድገትና ለአህጉራዊ ትስስር መሰረት የሚሆን አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።

በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እና የመነጨውን ኃይል ለተጠቃሚው ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ላይ ትኩረት ተሠጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ማከፋፈያ ጣቢያው 40 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃያል የማስተላለፍ አቅም እንዳለው የጠቆሙት ሚኒስትሩ ጣቢያው ለነጆ ከተማና አካባቢው ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ ባለፈ በአካባቢው የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።ባለሃብቶች በአካባቢው የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶችን በአግባቡ በመጠቀም አካባቢያቸውን እንዲያለሙም ዶ/ር ስለሽ ጥሪ አቅርበዋል።

ማከፋፈያ ጣቢያው 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመር እና አራት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ያሉት ሲሆን የተገነባውም በተቋሙ የትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኮንስትራክሽን የራስ ኃይል ቢሮ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ለማከፋፈያ ጣቢያው ከ65 ሚሊዬን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ ወጪውም በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ መሆኑ ተገልጿል።

ዛሬ በተካሄደው የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻን ጨምሮ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ አባ ገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች መገኘታቸውንም መረጃው ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም